አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24 2004 /ዋኢማ/– በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ የንግድ አሰራር እንዲሰፍን ለማስቻል የዘርፉን አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ዛሬ በንግድ መስፈርት ዝግጅትና በቴክኒክ ደንብ አስፈላጊነት ላይ ለንግዱ ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቷል፡፡
በሚኒስቴሩ የንግድ አሰራርና ሪጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓሊ ሲራጅ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የዘርፉን አቅም በማሳደግ የንግድ አገልግሎቱ በጥራትና በቅልጥፍና ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በንግዱ ዘርፍ ለተሰማሩ ተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የማይናቅ ለውጥ የታየ ቢሆንም ከነጋዴዎች ቁጥር ማደግና ከምርቶችና አገልግሎቶች ብዛትና ውስብስብነት መጨመር ጋር ተያይዞ የንግድ ስርዓቱ በሚፈለገው መጠን ህጋዊነትና ዘመናዊነትን የተከተለ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራት ጉድለት፣ በመጠቀሚያ ጊዜ ማለፍ፣ ተገቢ ባልሆነ የአመራረት ሂደትና አገልግሎት ምክንያት በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት በማድረስ አካባቢ እስከመበከል ለሚደርስ አደጋ ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም በንግዱ ዘርፍ የታዩትን ደካማ ጎኖችና ጉድለቶች ለማስተካከልና ለመቅረፍ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ አስፈልጓል ብለዋል፡፡
የቴክኒክ ደንቦችና አስገዳጅ ደረጃዎች ከተስማሚነት ምዘና ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ንግድን የሚደግፉ፣ የሚያበረታቱና የሚያቀላጥፉ መሣሪያዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በንግዱ ዘርፍ የሚታዩትን መሰረታዊ ችግሮችና የጥገኝነት አደጋዎች በማስወገድ ለልማታዊ ባለሐብቱ የተሻሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሸቀጦች የገበያ ዝውውር በአቅርቦትና በፍላጎት ህግጋት መሰረት እንዲመራ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የሸማቹን ህብረተሰብ ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የንግዱን ማህበረሰብና የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም መገንባት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠውም አስረድተዋል፡፡
በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል በህግ ማዕቀፍ የታገዘ ግልጽ፣ ፍትሃዊና ተጠያቂነት ያለው የንግድ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
የንግዱ ማህበረሰብ ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት እንዲሁም ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች በመከላከል የሀብረተሰቡን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች መስፋፋትን ከመግታት አንጻር ሚናው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫው የንግዱ ህብረተሰብ በአገሪቱ የተጀመረውን የንግድ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ፣ በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆን፣ ለሸማቹ ተስማሚ ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ መወዳደር እንዲችል የሚያደርግ ጠቃሚ ትምህርት እንደሚሰጥ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡