አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25 2004/ዋኢማ/– በተለያዩ አገሮች በዳያስፖራ ፖሊሲ ላይ በተደረገ ውይይት ጠቃሚ ግብዓቶች መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፖሊሲው ፀድቆ ሥራ ለይ ሲውል የተለያዩ አደረጃጀቶች እንደሚኖሩትም ተገልፆል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ማስፋፍያ ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር አቶ ፈይሰል አልይ ለዋልታ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚገኙባቸው ከሃያ በላይ በሚሆኑ የሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የአውሮፓ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በተደረገ ውይይት በርካታ ሀሳቦች ተነስተዋል፤ ጠቃሚ ግብዓቶችም ተገኝተዋል።
በደቡብ አፍሪካ በፕሪቶሪያና ጆሀንስበርግ ከተሞች በቅርቡ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ውይይት እንደሚደረግ የተናገሩት አቶ ፈይሰል የገና እና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የምክክር መድረክ ይዘጋጃል ብለዋል።
በረቂቅ ፖሊሲው ላይ እየተደረገ ያለው ውይይት ከሞላ ጎደል ተጠናቋል ያሉት ዳይሬክተሩ በቀጣይ በሁሉም መድረኮች የተነሱ ሃሳቦች ታይተው በፖሊሲው ውስጥ እንደሚካተቱ ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የዲያስፖራ ፖሊሲው ከዚህ በፊት መንግስት በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅሞች በሚመለከት ያወጣቸውን ሕጎች፣ መመሪያዎችና የማበረታቻ ማዕቀፎች ያካተተ ነው።
በመሆኑም ፖሊሲው ኢትዮጵያውያኑም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ የበለጠ እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ባሉበት አገር በኤምባሲዎችና በሚሲዮኖች አማካይነት ስለደህንነታቸውና መብቶቻቸው ለመከታተልም ያስችላል።
በተለይ ሰራተኛንና አሰሪን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች ከሚሲዮኖች ጋር ግንኙነት ኖሯቸው የላኩአቸውንና የተቀበሉአቸውን ሰራተኞች ለመከታተልና የተሟላ መረጃ ለመያዝ እንደሚያግዝም አቶ ፈይሰል ተናግረዋል።
ፖሊሲውን ተፈፃሚ ለማድረግ በቀጣይ ዝርዝር መመሪያዎችና ደንቦች እንደሚወጡ የገለፁት ዳይሬክተሩ በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊሲውን ተፈፃሚነት የሚከታተል የአማካሪ ምክር ቤት ይቋቋማል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሚሲዮኖችና ከመንግስት ጋር የሚያገናኝ የዳያስፖራ አማካሪ ምክር ቤት፣ የዳያስፖራ ብሔራዊ ካውንስልና በተለይ በሁሉም ክልሎች የዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች እንደሚቋቋሙም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በክልሎች የሚቋቋሙ የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች በክልሎች መካከል የሚታዩ መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዙ ከአቶ ፈይሰል ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።