አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26 2004 /ዋኢማ/ – የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አገሪቱ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የያዘቻቸውን ዕቅዶች ለማሳካት የሚያስችሉ አዳዲስ የትምህርት ኘሮግራሞችን ከፍቶ በማስተማር ላይ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቱን በምርምር ለመደገፍ በየዓመቱ የተለያዩ ይዘት ያላቸው የምርምር ውጤቶችን በማውጣት ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ዩኒቨርሲቲው በተለይ በህዝብ አስተዳደር፣ በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደርና በከተማ ኘላንናልማት በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የከፈታቸው አዳዲስ ኘሮግራሞች አገሪቱ የተያዘቻቸውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ለመተግበር ትልቅ ሚና አላቸው።
የመንግስት የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ የሚፈፀሙት ሕዝቡን ለለውጥና ለበለጠ ውጤት ማነሳሳት የሚችሉ ባለሙያዎች ሲፈጠሩ በመሆኑ በሕዝብ አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ የተከፈተው ኘሮግራምም ይህንኑ ክፍተት በመሙላት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ዩኒቨርሲቲው በመግለጫው አትቷል ።
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ውስን የሆነውን የሕዝብ ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የገለፀው ዩኒቨርሲቲው ለዚህም በሙያው በቂ ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል፤ ዩኒቨርሲቲውም የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር የትምህርት ዘርፍ ቀርፆ በሦሰተኛ ዲግሪ ደረጃ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ነው።
በከተማ ኘላንና ልማት ዘርፍ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የተቀረፀው የትምህርት ፕሮግራምም በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የከተሞች ቁጥር በፕላን ለመምራት የሚያስችሉ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያግዛል።
ዩኒቨርሲቲው የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቱን በምርምር በመደገፍም በየዓመቱ የተለያዩ ይዘት ያላቸው የምርምር ውጤቶችን በማውጣት ላይ መሆኑንም አስታውቋል ። በዘንድሮ ዓመትም በከተማ ልማት፣በፌዴራሊዝም፣ በህዝብ አስተዳደርና በመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር እንድሁም በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስታውቋል።
የአስፈፃሚ መስሪያቤቶችን የሰው ኃይል አቅም በመገንባትም ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ባለሙያዎች የአጫጭር ሥልጠናዎችን ይሰጣል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከዶክትሬት ድግሪ በተጨማሪ በመጀመሪያ ዲግሪ ሁለት፤ በሁለተኛ ዲግሪ ስምንት አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈቱንም በመግለጫው አሳውቋል።