የሲሚንቶ አቅርቦቱን 27 ሚሊየን ቶን ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አመት መጨረሻ ላይ አመታዊ የሲሚንቶ አቅርቦቱን ወደ 27 ሚሊየን ቶን ለማድረስ ታቅዶ የተለያዩ ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ እቅዱን ለማሳካት 37 አዳዲስና ነባሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የግንባታና የማስፋፊያ ስራዎችን ለማካሄድ ፈቃድ ወስደው ወደ ልማት ገብተዋል።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሲሚንቶ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቁጥር 15 እንደደረሰ የገለፁት አቶ መላኩ፤ ፋብሪካዎቹ ማምረት በመጀመራቸው 7 ሚሊየን 836 ሺ ቶን ሲሚንቶ ለገበያ በመቅረብ ላይ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ 12 ነጥብ 61 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ለገበያ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት አቶ መላኩ፤ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ያለውን የሲሚንቶ ዋጋ እንዲቀንስ እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት።

ፍቃድ ወስደው ወደ ልማቱ ከገቡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካከልም ሁለት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ 7 የሚሆኑ ፋብሪካዎች በዘንድሮው ዓመት መጨረሻ ላይ ማምረት ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ከመሄዷ ጋር ተያይዞ የሲሚንቶ ፍላጎቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ በመምጣቱ አቅርቦትና ፍላጎቱ እንዲራራቅ አድርጎታል።

መንግስት የሲሚንቶ አቅርቦቱን አስተማማኝ በማድረግ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ አመት መጨረሻ ላይ 27 ሚሊየን ቶን በማድረስና አጠቃላይ የነፍስ ወከፍ የሲሚንቶ ፍጆታውን ከ35 ኪሎ ግራም ወደ 300 ኪሎ ግራም በማሳደግ የተጀመረውን የኢኮኖሚ እድገት ከግብ ለማድረስ አቅዶ እየሰራ ነው።

ከአገሪቱ ፈጣን የልማት እንቅስቃሴና የኮንስትራክሽን ዘርፍ እድገት ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ የሲሚንቶ ምርት ፍላጎትን ሊያሟላ ባለመቻሉ ባለፉት አመታት በሲሚንቶ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ክፍተት መፈጠሩ ይታወቃል።

ክፍተቱን ለመሸፈንም መንግስት የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ከጀመረ የቆየ ሲሆን፤ ከተወሰዱት የመፍትሄ እርምጃዎች መካከልም ሲሚንቶን ከውጭ ማስገባትና ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመዘርጋት ልማታዊ ባለሀብቶችን በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ ይገኝበታል።