ለባዮ-ዲዝል ተክል ልማት ከ558 ሺ ሄክታር በላይ መሬት ተለየ

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2004 (ዋኢማ) – በአራት የሀገሪቱ ክልሎች የባዮ-ዲዝል ተክል ለማልማት የሚያስችል 558 ሺ 827 ሄክታር መሬት መለየቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ለባዮ-ዲዝል የሚያገለግል የጃትሮፋ፣ የካስተርና ሌሎች ተክሎችን በ558 ሺ 827 ሄክታር መሬት ላይ ለማስፋፋት የሚያስችለው መሬት የተለየው በትግራይ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልሎች ነው።

የተለየው መሬት በክልሎቹ በሚገኙ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በ27 ወረዳዎችና በአንድ ልዩ ወረዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 80ሺ ሄክታር መሆኑን ተናግረዋል።

ለባዩ-ዲዝል ልማት የሚሆነው የጃትሮፋ ተክል በአርሶ አደሩ አካባቢ ያለ እምቅ ሀብት ነው ያሉት አቶ ብዙነህ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል በ27 ወረዳዎች ከ75 ሚሊዮን በላይ የጃትሮፋ ተክል የሚገኝ ሲሆን፤ ከዚህም 93 ሺ 750 ኩንታል የጃትሮፋ ምርት ሊገኝ እንደሚችል ገልፀዋል።

በአማራ ክልልም በ13 ወረዳዎች በአርሶ አደሩ ማሳና ለአጥርነት የተተከለ ከ10 እስከ 11 ሚሊዮን የሚገመት የጃትሮፋ ምርት የሚገኝ ሲሆን፤ በአመት እስከ 275 ሺ ኩንታል የጃትሮፋ ምርት ይገኛል ብለዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በ23 ወረዳዎች የጃትሮፋ ተክል እንዳለ የገለፁት አቶ ብዙነህ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ምርቱን ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የጃትሮፋን ተክል አርሶ አደሩ በመጭመቅ ለማብሰያነትና ለመብራት እንዲጠቀምበት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው በባኮ ገጠር ቴክኖሎጂ ማዕከል ተመርቶ በደቡብ ክልል ስምንት ወረዳዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ቴክኖሎጂውን በመስክ ለመሞከርና በተጨማሪ ለማምረት በሂደት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ቴክኖሎጂው ተሞክሮ ውጤታማነቱ እንደታወቀ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ስልጠና በመስጠት እንዲያመርቱት ይደረጋል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የጃትሮፋ ምርትን በስፋት እንዲያመርተው ለማስቻልም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርቱን አርሶ አደሩ በማምረት ለገበያ እያቀረበው መሆኑንም ገልፀው፤ በዘርፉ ለመሰማራትም 83 ባለሀብቶች ፍቃድ መውሰዳቸውን ገልፀዋል።