ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 05 2004 /ዋኢማ/ – ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ላይ የጠበቀ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ 75 ሺ በላይ ሰዎች የቅድመ ጉዞ ሥልጠና ወስደው በህጋዊ መንገድ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና የባህረ ሰላጤ አገራት ለሥራ ተሰማርተዋል።

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት ሕገወጥ የሰዎች ዝውወርን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎችን አሰራር በቅርብ በመከታተል ላይ ይገኛል።

ኤጄንሲዋች በዘርፉ የወጡትን ሕጎችና አዋጆች እንዲሁም የተሰጣቸውን ፈቃድ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋላቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር እራሱን የቻለ ክፍል መቋቋሙን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በየጊዜው ሥራቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ተጠንክሮ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ግርማ ማብራርያ በአሁኑ ወቅት 178 ያህል የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ፈቃድ ወስደው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ባለፉት ስድስት ወራት በገቡት ውል መሠረት መስራት ሲገባቸው በሕገወጥ የሰዎቸ ዝውውር ተሰማርተው የተገኙ አራት ኤጄንሲዎች ፈቃድ ተሰርዟል።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ዜጎች ሕጋዊውን መንገድ ብቻ እንዲከተሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲ አዋጅ ወጥቶ ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በፌዴራል ደረጃ 13 መሥሪያ ቤቶችን ያሳተፈ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ፣በክልሎች በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ በተመሳሳይ በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባታቸውን አቶ ግርማ አስረድተዋል።

በየጊዜው ከባለድርሻ አካላት ጋር የችግሩን ስፋትና እየደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውንና የፌዴራል እና የክልል መስሪያ ቤቶችም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በዕቅዳቸው ውስጥ አካትተው እንዲንቀሳቀሱ ሰፊ ሥራ መሰራቱንም ዳይሬክቴሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የህገውጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከአጎራባች አገሮች በተለይም ከኬኒያና ከሱዳን ጋር በቅርቡ የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረሟንም አቶ ግርማ ተናግረዋል።

የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጮች በአብዛኛው ሴቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክቴሩ የሕገወጥ ደላላዎች ተፅዕኖ፣ የቤተሰብ ጫና እና በአገር ውስጥ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን አለማየት በዋነኝነት ተጠቃሽ መነሻዎች ናቸው ብለዋል።

በመዳረሻ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ የሚያጋጥሙአቸውን ችግሮች ለማስቀረት ሚኒስቴሩ የቅድመ ጉዞ ገለፃ በመስጠት ለይ ይገኛል።እንደ አቶ ግርማ ማብራርያ ከሐምሌ 01፤ 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ከ75 ሺ በላይ ሰዎች የቅድመ ጉዞ ሥልጠና ወስደው የሥራ ውላቸው ፀድቆ ወደ ዱባይ፣ኩዌት እና ሳዑዲ አረቢያ ተሰማርተዋል።

አንዳንድ ያነጋገርናቸው ሠልጣኞችም ትምህርቱ በማንኛውም ጊዜ ችግር ሲያጋጥማቸው ከኤምባሲዎች፣ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከላኩአቸው ኤጄንሲዎች ጋር እንዴት ግንኙነት መፍጠር እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥልጠና ባለሙያ የሆኑት አቶ ያሬድ አለማየሁ በበኩላቸው እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ዜጎች ወደ አረብ አገራት በሚሄዱበት ጊዜ የሚያጋጥሙአቸውን ችግሮች ለይተው እንዲያውቁና ከአሰሪዎቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያግዛል ብለዋል።

ከ 2002 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ 21 2004 ዓ.ም ድረስ ለ137 ሺ 126 ያህል ሰዎች የቅድመ ጉዞ ሥልጠና መሰጠቱንም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።