“የሂውማን ራይትስ ርዕዮተዓለማዊ ዘመቻ ከልማት ጉዟችን አያደናቅፈንም” የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 9 ቀን 2004 (ዋኢማ) – የሂውማን ራይትስ መሰረተ ቢስ ርዕዮተዓለማዊ ዘመቻ ከልማት ጉዟችን አያደናቅፈንም ሲል የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ትናንት ማምሻውን ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው  ሂውማን ራይትስ ዎች በመባል የሚታወቀውና የኢትዮጵያን ገጽታ ለማበላሸት እንቅልፍ እጥቶ የሚያድረው ድርጅት ዛሬም በጋምቤላ ዜጎችን ለተሻለ ሕይወት የማብቃት እንቅስቃሴን በመቃወም የሃሰት ሪፖርት አውጥቷል፡፡

ሪፖርቱ ሰፊ ዓለም ዓቀፍ ሽፋን ያገኝለት ዘንድ የሚቻለውን ያህል የሚድያ ስልቶችን ቀይሶ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በዚህ ዓይነት የቅጥፈት ዘመቻ ሲሰማራ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የጠቆመው  መግለጫው የመጨረሻውም እንደማይሆን  ለመገመት አያስቸግርም ብሏልል፡፡

በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሽፋን የሚንቀሳቀሰውና ከሌላው አገር በተለየ አኳኋን ኢትዮጵያን ጠምዶ የያዘው ሂውማን ራይትስ ዎች በተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ሪፖርት ማውጣቱ የተለመደ መሆኑንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡

እንደመግጫው ገለጻ በ2001 ዓ.ም. በኦጋዴን፣ በ2002 ዓ.ም. በፀረ-አሸባሪነት ህግ፣  በ2003 በድርቅና ዛሬ ደግሞ በጋምቤላ ሕዝብ የማስፈር ጉዳይ ላይ ከተጨባጩ እውነት ጋር የተጣላ፣ በሃሰት ውንጀላዎችና ስም የማጥፋት ዝባዝንኬ የተሞላ ሪፖርት አቅርቧል፡፡

ኢትዮጵያ አንዲት ሉዓላዊት አገርና ማንም የውጭ ሰው የማያሳድራት መሆኗ እየታወቀ ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው ድርጅት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ምን አግብቶት ሲፈተፍት እንደሚኖር ለታዛቢ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው ያለው መግለጫው  ይሁንና  ከኢትዮጵያውያን በላይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ተቆርቋሪ በመምሰል የኢትዮጵያን ገፅታ ጥላሸት የሚቀባው ያለ ምክንያት እንዳልሆነ መግለጫው ያትታል፡፡

የዘመቻው ባህሪ በትክክል ለመረዳት  በጋምቤላ ክልል ያለውን ሁኔታ  በማነጻጸር መመልከት ተገቢ ነው ያለው መግለጫው መንግሥት ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን ለማረጋገጥ በተለይ  ለዘመናት በተፈጸመባቸው አድሎ ምክንያት የእድገትና የተጠቃሚነት እድል ተነፍገው የኖሩ የታዳጊ ብሔረሰቦች ሕዝቦች በልዩ ትኩረት እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በመላ አገሪቱ ማንም ሳይጠቀምበት የኖረውና ሕዝብ ከሰፈረበት አካባቢ ውጪ ያለውን ለግብርና ልማት የተመቸ መሬት ለአገር ውስጥና ለውጭ አልሚዎች የመስጠት ስትራቴጂ የሚከተል ሲሆን በተበታተነ አሰፋፈር በከፊል አርብቶ አደርነትና በቁፋሮ የአስተራረስ ዘይቤ ዝቅተኛ ምርት እያመረቱ የሚኖሩ የታዳጊ ብሔረሰብ አባላትን በማስፈር የአመራረት ዘይቤያቸውን ለመቀየር እየሰራ ይገኛል ብሏል መግለጫው።

በጋምቤላ፣ በቤኒሸንጉል ጉሙዝና በደቡብ ክልሎች በፍጥነት ሊለማና አገራዊ እድገትንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋግጥ ሊውል ከሚችለው 3.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ከ425 ሺህ ሔክታር የማይበልጥ መሬት ለአልሚዎች በሊዝ መታደሉንም ጠቁሟል።

አልሚዎች ከወሰዱት መሬት መካከል እስካሁን 42 ሺህ ሔክታር መሬት ብቻ የለማ ሲሆን ይህም በሰፊው ሊለማ ከሚገባው መሬታችን 1.2 ከመቶ ብቻ ጥቅም ላይ መዋሉን እንደሚያሳይ መግለጫው ጠቁሞ ሂውማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያ በእነዚህ አካባቢዎች ልታለማውና ለሕዝቡ ጥቅም ልታውለው ከሚገባት መሬት ውስጥ ገና አንድ መቶኛውን ብቻ በተጠቀመችበት በዚህ ወቅት “የኢትዮጵያ መሬት ለውጭ ሰዎች ተቸበቸበ” ” መንግስት በአገሪቱ መሬት እየተጫወተ ነው” የሚል ሰፊ ዘመቻ ማካሄዱ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ በማሰብ እንዳልሆነ ከዚህ በላይ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ ሊቀርብ ይችላል።

ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋ አልምታ የሕዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በሚታደርገው ጥረትና ርብርብ ላይ ዘመቻ ማካሄዱ በርግጥም ሂዉማን ራይትስ ዎች ጠቡ ከኢትዮጵያ ልማትና ከህዝቦቿ ከልማቱ ተጠቃሚነት  ለመሆኑ ራሱን የቻለ ማረጋገጫ ነው ብሏል፡፡

መግለጫው አያይዞም መንግስት በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ ሕዝቦችን በማስፈር ወደ ተሻለ ኑሮ ለማሸጋገር በያዘው እቅድ እስካሁን 1 መቶ 25 ሺህ ቤተሰቦችን ያሰፈረ ሲሆን  20 ሺህ የሚሆኑት በጋምቤላ ክልል መሆኑን ጠቁሟል።

በጋምቤላ በ43 መንደሮች በተካሄደ የማስፈር እንቅስቃሴ 22 የጤና ኬላዎችን፣ 19 ትምህርት ቤቶችን፣ 72 የመስኖ ጠለፋዎችን፣ 407 የውሃ ፓምፖችን፣ 18 የእንስሳት ክሊኒኮችን መገንባታቸውን የጠቆመው መግለጫው 30 የእህል ወፍጮዎችን በመትከልና 128 ኪሎ ሜትር መንገዶችን በመስራት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ መሟላቱን ገልጿል።

የማስፈሩ ሂደት በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑም በዓመት ለማስፈር ተይዞ ከነበረው 15 ሺህ ቤተሰብ በላይ 20 ሺህ ቤተሰቦችን በፈቃደኝነት ማስፈር መቻሉም አስታውቋል።

ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሂዉማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያ “ኔዘርላንድስን የሚያክል መሬት ለአልሚዎች ሰጠች” ” ኢትዮጵያ አንዳችም ዝግጅት ባላደረገችበት ሰፋሪዎችን ወደ አዲሱ መንደር አስገባች” በማለት መሰረተ ቢስ ውንጀላን ለቅጥፈቱ ማስደገፊያ እስከማድረግ ደርሷል።

ድርጅቱ ሰሞኑን ለሚዲያ በበተነው የውንጀላ ጽሁፍ ላይ ” ሰፈራው ቃል በተገባው መሰረት የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተገነቡበት ሳይሆን ፈጽሞ ደብዛቸው በሌለበት አኳኋን የተካሄደ ነው” እስከማለትም ደርሷል።

ይህ ድርጅት የጋምቤላን መሬት ለምነትና ክልሉ በዝናባማነታቸው ከሚታወቁ የአገራችን ክልሎች ዋናው መሆኑን በመሸፈን ” አዲሱ ሰፈራ በተካሄደበት መንደር የሚገኘው መሬት ደረቅና ለምነቱ የተሟጠጠ ነው” በማለት አይን ያወጣ ቅጥፈት ጨምሮበታል ብሏል መግለጫው።

መንግስት በተፈጥሮ በታደለ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ለሚካሄድ የመስኖ ልማት አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን መርጦ ማስፈሩን በመደበቅ ጋምቤላ ላይ ስለ ድርቅና የመሬት ለምነት መሟጠጥ የሚያወራዉ ሂዩማን ራይትስ ዎች በእርግጥ ለዘመቻዉ የሚያግዘዉ እስከሆነ ድረስ ያልተጣራ መረጃና ነጭ ዉሸት ይዞ መዝመቱ  እንደማያስጨንቅም መግለጫው ጠቁሟል።

እነዚህ ሁሉ ተደጋጋሚ መሰረተ ቢስ ዉንጀላዎች ድርጅቱ ኢትዮጵያን እንደብቸኛ ጠላት አገር ወስዶ እየዘመተባት እንደሆነ የሚያረጋግጡ መሆኑንም መግለጫው ያሳያል።

መግለጫው በመጨረሻም  ሂውማንራይትስ ዎች ከተጠቀመበት የሊበራል ርዕዮት ከሚያራምደው የጥፋት ፖሊሲ በቀላሉ እንደማይላቀቀው ሁሉ ኢትዮጵያና ሕዘቦቿም ከተያያዙት ልማታዊ አቅጣጫ እንዲህ በቀላሉ ይላቀቃሉ ብሎ መጠበቅ ከንቱ ምኞት መሆኑን አመልክቷል፡፡