ጠ/ሚ መለስ በሱዳኖች መካከል በነዳጅ መስመር ላይ ያለውን አለመግባባት እንዲፈቱ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 10 ቀን 2004 (ዋኢማ) – በሁለቱ ሱዳኖች መካከል በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ያለውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥረት እንዲያደርጉ ደቡብ ሱዳን ጠየቀች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም አለመግባባቱ በአጭር ጊዜ የሚፈታበትን መንገድ ከሌሎች የኢጋድ አባል አገራት ጋር በመመካከር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ሜይ አርዲት ልዩ መልእክተኛ ሚስተር ኢማኑኤል ላዊላን ዛሬ ምሽት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ልዩ መልእክተኛው ሚስተር ኢማኑኤል ላዊላ በሁለቱ ሱዳኖች መካከል በነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ ያለውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ኢትዮጵያ በርካታ አስተዋጽኦዎችን ማድረግ እንደምትችልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካረጋገጠች በኋላ በአፈፃፀም ላይ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች አስረድተው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

አለመግባባቱን ለመፍታት የሚደረገው ድርድር ቀጥሎ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስም የተቋረጠው ነዳጅ መተላለፍ እንዲቀጥልና ሁለቱ አገሮች የሚስማሙበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚሹም አመልክተዋል፡፡

በተለይ በነዳጅ አቅርቦት በኩል የተከሰተውን አለመግባባት በማጤን የሁለቱ አገራት ወዳጅ እንደመሆናቸውና ቀደም ሲል የኢትዮጵያን ድጋፍ ሲያገኙ እንደነበረ ሁሉ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከሌሎች የኢጋድ አባል አገራት ጋር ተባብረው ችግሩን እንዲፈቱ ለመጠየቅ መምጣታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር እንደመሆናቸውና እንደ ጐረቤት አገርም አለመግባባቱ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ የሚፈታበትን መንገድ ከሌሎች የኢጋድ አባል አገራት ጋር በመመካከር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበትን አጋጣሚ በመጠቀም ምክክር በማድረግ ችግሩን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን አገራት ችግር ለመፍታት በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ መሪነት የተቋቋመው ፓናል ብዙ ጥረት እያረገ መሆኑን ጠቁመው ይህንን እና የአፍሪካ ሕብረትን ጥረት ኢጋድ ሊደግፍ የሚችልበትና ከፓናሉ ጋር አብሮ የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚያመቻቹ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ (ኢዜአ)