የተንዳሆና የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች በመጪው ጥቅምት ወደ ምርት ይገባሉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 12 2004 /ዋኢማ/ – አዲሱ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ እና በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ እየተካሄደ ያለው የማስፋፊ ግንባታ ተጠናቆ በመጪው ጥቅምት ወር ስኳር ማምረት እንደሚጀምሩ የፋብሪካዎቹ ሥራ አስካጆች አስታወቁ።

የፋብሪካዎቹ ኃላፊዎች ሰሞኑን ከመንግስት እና ከግል የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች ፋብሪካዎቹን በጎበኙበት ወቅት እንዳስታወቁት የፋብሪካዎቹ ግንባታ እና የማስፋፊያ ሥራ በአሁኑ ወቅት ከ60 በመቶ በላይ ተጠናቋል።

በመሆኑም ፋብሪካዎቹ  ከሚቀጥሉት አስር ወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ምርት የማምረት ሥራ ይጀምራሉ።

የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የፕሮጄክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ለማ ጉርሙ እንደገለፁት የፋብሪካው የማስፋፊያ ሥራ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት በመደበው 346 ሚሊዮን ብር እና ከህንድ መንግስት በተገኘ የ125 ሚሊዮን ዶላር ብድር ነው።

ፋብሪካው በሰኔ ወር በሙከራ ደረጃ አገዳ የመፍጨት ሥራ ይጀምራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን 7 ሺ 350 ኩንታል ስኳር እንደሚያመርት ተናግረዋል።

እንደ አቶ ለማ ማብራሪያ ፋብሪካው ከስኳር ምርት በተጨማሪ በአዲስ መልክ ከሚገነባው የኢታኖል ፋብሪካ በቀን 20 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል።

ለስኳር ፋብሪካው በዋና ጥሬ ዕቃነት የሚያገለግለው የአገዳ ምርት በ10ሺ ሄክታር ላይ በመንግስት እና በማህበር በተደራጁ አርሶአደሮች አማካይነት እየለማ መሆኑንም አቶ ለማ ጠቁመዋል።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የኦኘሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ዘነበ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኘው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ የማምረት ሥራውን በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም ይጀምራል ብለዋል።
እንደ አቶ እንዳልካቸው ማብራሪያ ፋብሪካው በመጀመሪያ ምዕራፍ 13ሺ ቶን የሸንኮራ አገዳ በቀን በመፍጨት 13ሺ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም አለው።

የሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን 26ሺ ቶን አገዳ በመፍጨት 26 ሺ ኩንታል ስኳር እንደሚያመርትም ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዓማታዊ አጠቃላይ የምርት አቅም 600ሺ ቶን ስኳር መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ጠቁመው ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን አስረድተዋል።

ፋብሪካው ከስኳር ምርት በተጨማሪ 63 ሺ ኪሎ ሊትር ኢታኖል በማምረት በቀን 70 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለውም ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

ለፋብሪካው የምርት ግብዓት ወደፊት በ50 ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ልማት እንደሚካሄድ አቶ እንዳልካቸው ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት በ18 ሺ ሄክታር ላይ ልማቱ በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል።

የፋብሪካዎቹ ኃላፊዎች እንደገለፁት የሁለቱ ፋብሪካዎች የግንባታ እና የማስፋፊያ ሥራ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ሂደት መግባት፤ የአገሪቱን የስኳር ምርት አቅርቦት ከማሟላት በተጨማሪ አገሪቱ ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት ያቀደችውን ለማሳካት ያግዛል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አስር የስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት በአለም አቀፍ የስኳር ገበያ ውስጥ ያላትን ድርሻ ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ የማድረስ እቅድ እንዳላት ይታወቃል።