በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳንና በጅቡቲ መንግስታት መካከል የመሰረተ ልማት ግንባታ የስምምነት ፊርማ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ጥር 25 2004 /ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳንና በጅቡቲ መንግስታት መካከል የመሰረተ ልማትን መገንባት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ ትናንት ማምሻውን ተካሄደ።

በአገራቱ መካከል የተካሄዱት ስምምነቶች በሶስቱ ሀገራት መካከል በኢነርጅና በፋይበር ኦፕቲክስ ረገድ ትብብር ማድረግ የሚያስችሉ እና በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መንግስታት መካከል በመሰረተ ልማት ግንባታ ረገድ የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ ናቸው።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የመንገድ፣የባቡር፣የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን መስመር ለመዘርጋት ፕሮጀክቶችን በጋራ ቀርፀው እንደሚሰሩ ተነጋግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጁቡቲም በኤሌክትሪክ ሀይልና በፋይበር ኦፕቲክስ ዝርጋታ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሶፊያን አህመድ የጁቡቲ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ ኤሌያስ ሞላ ሮበሌህ እና የደቡብ ሱዳን ገንዘብ ሚኒስትር ኮስቲ ማሂሊ ናቸው፡፡

ሶስቱ ሀገራት በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፍ በጋራ ለመስራት መወሰናቸው የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ አካባቢያዊ ትስስር ለማጠናከር ያወጣውን ዕቅድ ተግባራዊነት ያፋጥናል ብለዋል፡፡

 በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዋሲሁን አባተ ለፋና እንደገለፁት ስምምነቶቹ የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ናቸው።

በቅርቡም የሶስቱ ሀገሮች የቴክኒካል ቡድኖች በአፈጻጸም ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ በፊት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶቻቸው ካደጉ ሀገራት ብቻ እንደነበር አስታውሰው ይህ ስምምነት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር በሀገራቱ መካከል ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድዋል። ኢትዮጵያም ምርቶቿን ለሀገራቱ በመላክ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል።

የስምምነቱን አፈጻጸም ለመከታተልም የጋራ ኮሚሽን እንደሚቋቋም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል። የጋራ ኮሚሽኑ ተሰብስቦ ከሶስቱ ሀገራት የተውጣጣ ቴክኒካል ኮሚቴዎችን ይሰይማል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ወደ ደቡብ ሱዳን ገብተው በሰፊው እንዲሳተፉ እና ለዚህም ዝግጁነት መኖሩን የአገሪቱ መንግስት መግለጹን መናገራቸውን ከኤፍ ቢ ሲ እና ከኢሬቴድ ያገኘነው ዘገባ ያስረዳል።