ፋብሪካው የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገለጹ

አዲስ አበባ, ጥር 28 ቀን (ዋኢማ) – ደርባ የሲሚንቶ ፋብሪካ አገሪቱ የተያያዘችውን የኢንዱስትሪ ልማት ለማፋጠን ክፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል በጫንጮ ከተማ አቅራቢያ የተገነባውን በ351 ሚሊዮን ዶላር የተገነባውን ፋብሪካ ሲመርቁ እንደተናገሩት የፋብሪካው ግንባታ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ያግዛል።

በዚህም እያደገ ከመጣው ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ፍላጎት በማሟላት ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

ፋብሪካው በዓመት ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው በመሆኑ፤አሁን ያለውን የአገሪቱ የሲሚንቶ ምርት መጠን ከዘጠኝ ሚሊዮን ቶን በላይ እንደሚያደርሰው አቶ መለስ ገልጸዋል።

ፋብሪካው በሲሚንቶ ምርት በኩል የሚታየውን ክፍተት በመሙላት ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ያም ሆኖ በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ልማትና ፍላጎት አንጻር አሁንም ተጨማሪ ፋብሪካዎች እንደሚጠይቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መግለጻቸውን ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል።

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በበኩላቸው በዚሁ ወቅት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት አዲሲቱን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ወጣቱን በማብቃት በአገሩ ልማት እንዲሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆን ስትራቴጂ እንደሚተገብርና በዚህም የአገሪቱ ዓበይት ችግሮችንና ፈጣን ልማትን ታሳቢ ያደረገ መርህ እንደሚከተል አስታውቀዋል።

ግሩፑ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በ100ቢሊዮን ብር ካፒታል የጂፕሰምና የእብነ በረድ ማምረቻዎች በተጓዳኝ እንደሚያቋቋም ሼክ አል አሙዲን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በሞጣና ደጀን ከተሞች እያንዳንዳቸው በቀን 40ሺህ ኩንታል የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ይቋቋማሉ ብለዋል።

ፋብሪካው በ123ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣በግንባታው ወቅት ከ5ሺህ 500 በላይ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ተሳትፈውበታል።

ፋብሪካው ለ500 ቋሚና ለአንድ ሺህ አምስት መቶ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። (ኢዜአ)