ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ግንኙነቷን ለማሳደግ እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥር 30 2004/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ እየተጫወተች ያለውን ሚና የሶማሌ ላንድ ፕሬዚዳንት አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትናንት የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት አህመድ መሐመድ ማህሙድ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ሲያነጋግሩ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ ከአገሪቱ ጋር ያላት ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ትሻለች።

ሁለቱ አገሮች በተለይ በጸጥታ፣በኢኮኖሚና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር በማጎልበትተጠቃሚነታቸውን ማስፋት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን አስታውቀዋል።

ሶማሌ ላንድ በቅርቡ በለንደን ከተማ በዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ በሚመክረው የሶማሊያውያን ጉባዔ ላይ በመሳተፍ ገንቢ ሚና እንድትጫወትም ጠቅላይ ሚኒስትር ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንት ማህሙድ  ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አገራቸው ከጎረቤቷ ጋር ያላትን ወዳጅነት የጋራ ትብብርን ለማጠናከርና ግንኙነቷን ለማጎልበት እንደምትሻለች አስታውቀዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ በሰፊው መወያየታቸውንና በዚህም የአካባቢ ጸጥታና ደህንነት፣ንግድና ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮች መዳሰሳቸውን ገልጸው፣በውይይቱ በተደረሰበት መግባባት መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ከዚህ ቀደም በተደረሱ ስምምነቶች አፈጻጸም ላይ መነጋገራቸውንም ፕሬዚዳንት ማህሙድ አስረድተዋል።

አገሮቹ ያላቸው ግንኙነት በመልካም ደረጃ ላይ የሚገኝ፣በወዳጅነትና በትብብር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አገራቸው እርካታ እንደሚሰማትም አስታውቀዋል።

አገራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅርቡ ተቀባይነት እንደሚያገኝም ፕሬዚዳንቱ እምነታቸውን መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉር ብሎም በአፍሪካ ባላት ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላት አገር በመሆኗም ፕሬዚዳንት ማህሙድ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ሶማሌ ላንድ በሶማሊያ ከዚያድ ባሬ አገዛዝ መውደቅ በኋላ ከተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ራሷን አግልላ ያወጣችና ነጻ አገር ሆና ለመታወቅ ጥረት ያደረገች አገር ነች።