በጥራጥሬ፣በቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 03 2004 /ዋኢማ/ – በጥራጥሬ፣በቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ የሚመከር የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በዚህ ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ ፣ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይሌ በርሄ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጥራጥሬ፣በቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ የሚመከር በአፍሪካ አህጉር የመጀመሪያ የሆነው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከየካቲት 19-21 ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡

ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተዘጋጀው በዚህ ጉባዔ ላይ ከአውሮፓ፣ከአሜሪካ፣ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአገር ውስጥ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዓለም አቀፍ ጉባዔው ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ኃይሌ በጉባኤው ላይ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎች፣ የተጋበዙ የምርት ተቀባዮች፣አምራች አገሮች፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ግዙፍ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ ላይ ዘርፉን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚስተናገዱም ሰብሳቢው ተናግረዋል።

አቶ ኃይሌ እንዳሉት የኢትዮጵያ ምርቶች ዋነኛ ገዥ የሆኑ ነጋዴች ምርቶቹ ወደሚመረቱበት አካባቢ በመሄድ ምርቶቹን ብቻ ሳይሆን፤ የአገሪቱ አጠቃላይ ገጽታ በራሳቸው መንገድ እንዲረዱም ሁኔታዎች ይመቻቻሉ።

ጉባዔው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ነባር ደንበኞችንና አዳዲስ ገዥዎች ያካተተ በመሆኑ፤ ለአገራችን ምርቶች ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ለማጠናከርና  አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተገልፆአል።
በንግድ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት የተመዘገቡ 150 ጥራጥሬ፣ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ላኪ ኩባንያዎች 40 የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።