ምክር ቤቱ ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን የሚያበለጽጉ 15 ዓዋጆች አጸደቀ

አዲስ አበባዕ የካቲት 8/2004 (ዋኢማ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፉት ስድስት ወራት ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን የሚያበለጽጉ 15 ዓዋጆች ማጽደቁን ዛሬ አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ አሰራሩን አደረጃጀሩን ሕዝባዊ ለማድረግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

የምክር ቤቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፉ ገብረአምላክ በሰጡት መግለጫ ምክር ቤቱ ዓዋጆቹን ያጸደቀው በቋሚ ኮሚቴዎች ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዓዋጆቹን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግና ከግልጽነት አንጻር በአጸዳደቃቸው ሂደት ላይ ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍና ሂደታቸውን እንዲከታተል መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ካወጣቸው ዓዋጆች መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣ ዓዋጅ፣የከተማ ቦታን በሊዝ የመያዝ ፣ የዓለም ዓቀፍ ቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት ኮንስቲትዩሽንና ኮንቬንሽን ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ለማጽደቅ የወጡት ይጠቀሳሉ፡፡

እንዲሁም የኢፌዴሪ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን፣ ለመስኖ፣ ለመንገድና ለከተሞች የብድር ስምምነት፣የእንስሳትና መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ለማጽደቅ የወጣና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ዓዋጆች ይገኙበታል፡፡

ምክር ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በሚመለከት ቋሚ ኮሚቴዎች ከ100 በላይ የሚሆኑ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን እቅድ አፈጻጸም መገምገሙን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ባደረጓቸው የመስክ ጉብኝቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ጠንካራ ጎኖች እንዲጎለብቱና ክፍተቶች የሚሞሉባቸው መንገዶች እንዲመቻቹ መደረጉንም ወይዘሮ አሰፉ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ኤጀንሲዎች በመደበኛ ስብሰባዎች ሪፖርት ያቀረቡባቸውን ግብዓቶች ለአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ተሰጥተዋል፡፡

ምክር ቤቱ 17 መደበኛና ሁለት ልዩ ስብሰባዎች፣ በቋሚ ኮሚቴዎች ከ100 በላይ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማዎችና 29 የመስክ ጉብኝቶች መከናወናቸውንም ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

በእስያ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና ከሌሎች አገሮች ጋር በፓርላማ ሥራ ላይ የልምድ ልውውጥ በማድረግ የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ጥረት ተደርጓል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ወር በጀመሩት የዕረፍት ጊዜያቸው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ለመወያየት ወደ ምርጫ ክልላቸው በመሄድ የውክልና ተግባራቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በዋናነት የሚያከናውናቸው ተግባራት ሕግ የማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የውክልና ሥራዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሯ አመልክተዋል፡፡

እነዚህን ቁልፍ ተግባራት ተግባራዊ ለማከናወን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን መሠረት ያደረገ የአምስት ዓመት ስትራተጂ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

የምክር ቤቱ አደረጃጀትና አሰራርን ቀልጣፋ ለማድረግ መሠረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥን ወደ ሙሉ ለመተግበር ለምክር ቤቱ አባላትና ለጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች የአቅም ግንባታና ሙያዊ ድጋፍ መደረጉን ኢዜአ አስታውቋል፡፡