አስተዳደሩ ለሕዝቡ ግልጽና ተደራሽ መረጃ በማቅረብ መልካም አስተዳደርን ለመገንባትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ይሰራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2004 (ዋኢማ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማው ሕዝብ ግልጽና ተደራሽ መረጃ በማቅረብ መልካም አስተዳደር ለመገንባትና የተጠያቂነትን መንፈስ ለማዳበር እየሰራ መሆኑን ዛሬ አስታወቀ፡፡

በአስተዳደሩ የመንግሥት መረጃ አቅርቦትና ስታንዳርዳዜሽን ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከአስተዳደሩ ኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የ20 መሥሪያ ቤቶችን ድረ-ገጾች በይፋ አስመርቋል ፡፡

የከንቲባውና የአገር ውስጥና የውጭ ግንኙነት አማካሪ አቶ ከፍያለው አዘዘ በምረቃው ላይ እንደተናገሩት ነዋሪዎች አስተዳደሩ መረጃ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሕዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነትንማረጋገጫ ተገንዝቦ በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

መረጃ ለዴሞክራሲያዊው ሥርዓት ዋነኛ መሣሪያ የግልጽነትና የተጠያቂነት ሥርዓት መገንቢያ መሆኑም ታምኖበት እየተሰራበት ነው ብለዋል።

ነዋሪዎች መረጃ የማግኘት መብታቸውን ተጠቅመው የመሥሪያ ቤቶቹን የሥራ ክንውኖችን ለመቆጣጠርና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰድ መጠየቅ እንደሚችሉም አቶ ከፍያለው አስረድተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የዜጎችን መረጃ የማግኘት፣ የማስተላለፍና የማሰራጨት ነፃነት ከማረጋገጥ አኳያ አስተዳደሩ ይህንኑ የሚያስተገብር ጽሀፈት ቤት አቋቁሞ በመንግሥት ተቋማት መረጃ እንዲደራጅ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ መረጃ በተለያዩ መንገዶች ለኅብረተሰቡ ለማድረስ እንዲቻል ተቋማት የየራሳቸው ድረ ገጽ እንዲኖራቸው ከአስተዳደሩ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ድረ ገጾቹን ማቋቋሙንም አስረድተዋል።

ኤጀንሲው የተቋማትን ድረ ገጽ የማበልፀግ፣ የመረጃ ቋት /ሰርቨር/ የማስገንባት፣ የኔትወርክና የመረጃ ሶፍት ዌር ሥራዎች አከናውኗል፡፡

በአጭር ጊዜ ለበርካታ መሥሪያ ቤቶች ድረ ገጸች መከፈቱ ለመረጃ የተሰጠውን ትክረት እንደሚያሳይ አማካሪው መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡

የድረ ገፆቹ በአንድ ላይ መመረቅ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ የተጀመረውን የመረጃ ስርጭት አቅም ያሳድገዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ሁሉም የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የድረ ገጽ ባለቤት እንዲሆኑና የአስተዳደሩ አንድ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ከፍያለው አሳስበዋል፡፡

በመረጃ አያያዝ፣ አደረጃጀት፣ አሰረጫጨት ሥራዎች ላይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣትም ጥረቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

አዲስ የተከፈቱት ድረ ገፆች በአዳዲስ መረጃ እየበለፀጉ፣ የተጠቃሚውን ግብረ መልስ እየሰበሰቡና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየታገዙ የሚሄዱ እንዲሆኑ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በትጋት እንዲሰሩ አማካሪው አስገንዝበዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሎዳሞ በበኩላቸው አስተዳደሩ መረጃ ለኅብረተሰቡ እንዲደርስና ማንኛውም የመንግሥት አካል መረጃ የመስጠት ግዴታውን በማወቅ መረጃ ለኅብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ማስተላለፍ የሚያስችል ሥርዓት እየዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሥራውን እውን ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ድረ ገፆችን ማበልፀግ ቀዳሚው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ድረ ገጾቹን ለማስመረቅ የተቻለውም በዚሁ ጠንካራ የትብብር መንፈስ ነው ብለዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ የከተማውን የመረጃ ሥርዓት መልክ ለማስያዝና የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ትግበራ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተጠናክሮና ተቀናጅቶ የሚሰራ እንደሆነም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡