በከተማው ሥር ነቀል ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ለውጥ ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው አስታወቁ

አዲስ አበባ, የካቲት 9 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) – በከተማው በሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ላይ የተጀመረውን ትግል በሥር ነቀል ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ለውጥ ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዛሬ ገለጹ።

ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ዛሬ የምክር ቤቱን አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት የግማሽ ዓመት ሪፖርት ላይ እንደተናገሩት አስተዳደሩ የከተማውን ዓበይት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ሥራዎችን ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንቅስቃሴ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።

ይህንንም ለማከናወን የአቅም ግንባታ የማስፋት ሥራዎችን በማጠናከርና የልማት ሠራዊትን በመፍጠር ሥር ነቀል ኅብረተሰባዊ ጉዞውን መሠረት ለማስያዝ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል።
አስተዳደሩ የልማት አጀንዳዎችንና ምርጥ ልምዶችን የመቀመር የለውጡን አድማስ የማስፋትና በሂደቱም በውጤቱም ሕዝቡን ተሳታፊም ተጠቃሚም ለማድረግ ጥረት መደረጉን ከንቲባው አስረድተዋል።

”ዋነኞቹን የርብርብ መስኮች ለይተን በእነርሱ ላይ ከመረባረብ ጎን ለጎን ሌሎቹን ዓበይት የልማት ዘርፎች ከቁልፍ ተግባራቱ በሚገኙ ልምዶችና የየራሳቸውን መደበኛ አሰራር እያሳለጡ ለማንቀሳቀስ ስልት ተቀይሷል” ብለዋል።

በዚህም ልዩ ትኩረት በተሰጠው የሥራ ዕድል ፈጠራ 33 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በማሰማራት ከ199 ሚሊዮን ብር በላይ መሰጠቱን አቶ ኩማ
አስረድተዋል፡፡

ብድር የማቅረብ ጉዳይ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ቢሆንም ብቻውን ውጤት እንደማይኖረው በመተማመን ዜጎች የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ በተደረገው ጥረት ከ144 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቆጥቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የኢንተርፕራይዞችን አፈጻጸም መመሪያ መሠረት በማድረግ ጀማሪ፣ ታዳጊ፣ የበቃና ታዳጊ መካከለኛ በሚል ከዘጠኝ ሺህ ለሚበልጡ ኢንተርፕራይዞች ደረጃ ተሰጥቷል፡፡

እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎችን አምራች ዜጎች ለማድረግ በተደረገው ጥረት 628 የሚደርሱ በጥርብ ድንጋይ መጥረብና ማንጠፍ ሥራ ሰልጥነው መመረቃቸውን ገልጸው፣በራሳቸው ምርጫ ፕሮጀክት አቅርበው ዘላቂ ሕይወታቸውን የሚመሩበት ምቹ ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

እነዚህ ወገኖች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውንም አቶ ኩማ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በአመለካከት፣ በክህሎትና በሥራ ባህል ማጎልበቻ ሥራዎች አሰልጥኖ ወደ ተጨባጭ ተግባር ለማስገባት ዝግጅቱ መጠናቀቁ አስታውቀዋል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት ከመሬትና መሬት ነክ ጋር ተያይዞ ያሉ ፀረ ልማት አመለካከትና ተግባሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት መደረጉ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያስረዳል።
የተቀናጀ የቤት ልማት ፕሮግራም በትክክለኛው አቅጣጫ የተራመደበት፣ የውሃና የመንገድ ሽፋን እያደገ የመጣበት፣ የትምህርትና ጤና ማዕቀፎች ለውጥ እያስመዘገቡ መምጣታቸውንተናግረዋል፡፡

የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታቦር ገብረ መድህን በበኩላቸው በከተማው የተጀመረውን የልማት፣የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠልበየደረጃው የምክር ቤቱ አባላት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ሕጎችን በማውጣት፣ አስፈጻሚውን በመደገፍ፣ በመከታተልና በመቆጣጠር የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ጉባዔው ለሁለት ቀናት ቆይታው የሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ተወያይቶ የሚያጸድቅ ሲሆን፣አምስት ረቂቅ ዓዋጆችና አንድ ደንብን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዳኝነት በተነሱ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የሚያጸድቅ ሲሆን፣የምክር ቤቱን ምክትል አፈ ጉባዔና የቋሚ ኮሚቴ ዎች አባላትን እንደሚሰይም መርሐ ግብሩ እንደሚያመለክት ኢዜአ አስታውቋል።