የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጥነቱን ጨምሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2004 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። እጥረቱን ተከትሎም ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሕዝቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በፈረቃ ሲያገኝ ቆይቷል። ይህም ሕዝቡን ምሬት ውስጥ ጥሎት ቆይቷል። በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይም ያሳደረውን ጫና መገመት አያዳግትም።
የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጐት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

የኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋትና ኢኮኖሚን ለማሳደግ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ማሟላት ቀዳሚ ሥፍራ ይሰጠዋል። የኃይል እጥረቱን ለመፍታትና በአንፃሩ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለማረጋገጥ መንግሥት ትልልቅ ሥራዎችን አከናውኗል።

ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እየመደበ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ገንብቷል። እየገነባም ይገኛል። በተለይ የአምስት ዓመቱ መርሐ ግብር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ ግቦች ተቀምጠው እየተሰሩ ነው። ከእነዚህ ግቦች ውስጥ አንዱ በዕቅድ ዘመኑ (2007 ዓ.ም) መጨረሻ ላይ ሀገሪቱን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ማሸጋገር ነው። ይህን ግብ ለማሳካት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ሥፍራ ይሰጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ከሚሰሩ የኤሌክትሪክ የኃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ እና ግዙፉ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ነው። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም አሥረኛ ደረጃን የሚይዘው ይኸው ግድብ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ አምስት ሺ 250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል። የግድቡን ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባስቀመጡት የመሠረት ድንጋይ ተጀምሯል። ይሄንን ተከትሎም ሕዝቡ ከፍተኛ መነሳሳት አሳይቷል። ሕዝቡ ግድቡን በራስ አቅም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በገንዘብም ሆነ በጉልበት የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ ቃል ገብቷል። በዚህ መሰረትም አሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦውን እያበረከተ ይገኛል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብም የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ የግድቡ ግንባታ አልተስተጓጐለም። የግድቡ ግንባታ እንቅስቃሴም በየጊዜው ለሕዝብ እየተገለጸ ነው። በአሁኑ ጊዜም የግድቡ ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚል ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲቪል ሥራዎች ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አቅርበንላቸዋል።

ኢንጅነር ስመኘው እንዳሉት፤ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የሲቪል፣ የኃይድሮና ኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታ ሥራዎችን በዋነኛነት ያካተተ ነው። እነዚህ ሥራዎች በተጓዳኝነት እየተሰሩ ናቸው። ግድቡ የሚገነባበት ቦታ እየተቆፈረ ይገኛል። እስከአሁንም አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ ልልና ድንጋያማ አፈር ተቆፍሮ ተነስቷል። ይህም ግድቡ የሚያርፍበት አስተማማኝ የመሰረት ወለል ለመድረስ የሚያስችል ነው።

የግድብ ቁፋሮ ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፋጠነ ነው ይላሉ። እስከአሁን ድረስም አንድ ሺ 780 ሜትር ርዝመትና 145 ሜትር ቁመት መቆፈሩን ይናገራሉ። ከቁፋሮ ሥራው በተጓዳኝም ከወንዝ ጠለፋ ጋር የተገናኙ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ነው የገለጹት። በተለይ የኃይድሮ መካኒካል ሥራዎች ማለትም ውሃ ከግድቡ ተቀብለው ወደ ኃይል ማመንጫው የሚያደርሱ፤ እንዲሁም ወደ ኃይል ማመንጫው የሚሄደውን ውሃ የሚቆጣጠሩና መሰል ሥራዎችን ከሲቪል ሥራው ጋር በማቀናጀት እየተሰሩ መሆናቸውን ነው ኢንጂነር ስመኘው የገለጹት። በአሁኑ ሰዓትም እነዚህ ሥራዎች ግምት ውስጥ ገብተው በዲዛይኑ መሠረት በምዕራፍ ተከፋፍለው ወደሥራ እየተገባባቸው ነው ብለዋል።
እንደ ኢንጅነር ስመኘው ገለጻ፤ ከሥራ ውሉ አንፃር የግድቡ ግንባታ ሥራዎች በጥሩ መልኩ በመጓዝ ላይ ናቸው። አቅምን በሰው ኃይልና በመሳሪያ ለማደራጀት ከፍተኛ ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ራስን በመሣሪያ ከማደራጀት አኳያ የከባድ መሣሪያዎች ግዥ እየተፈጸመ ነው። ተገዝተው በመጓጓዝ ላይ ያሉም አሉ። ግንባታው ቦታ ደርሰው አገልግሎት ላይ የዋሉም እንዲሁ።

በመሣሪያ መደራጀት የግድብ ግንባታ ሥራውን በላቀ ቅልጥፍና ለማከናወን ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ይገልጻሉ። ለአብነትም ከዚህ ቀደም የነበሩ መሣሪያዎች ውስን በመሆናቸው በወር አነስተኛ ሜትር ኩብ ሲቆፈር እንደነበር መጥቀስ ይቻላል ነው ያሉት። ሥራውን ሊያፋጥኑ የሚችሉ የተለያዩ መሣሪያዎች አገልግሎት መስጠታቸውን ተከትሎ ግን በቀን እስከ 13ሺ ሜትር ኩብ ያህል ልልና ድንጋያማ አፈር መቆፈርና ማንሳት መቻሉን ነው የተናገሩት። በሰው ኃይልም ሆነ በመሳሪያ ከቀን ወደ ቀን አቅም እየተጠናከረ መሄዱም ሥራውን ማፋጠን ተችሏል ሲሉም ገልጸዋል።

ከእነዚህ ሥራዎች ጐን ለጐንም ተጨማሪ የከርሰ ምድር ጥናቶች እየተደረጉ ነው። ግድቡ የሚያርፍበት ቦታ ውሃ እንዳይሰርግ ወይም እንዳይሰርጽ ችግር ካለም የኢንጅነሪንግ መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ የፍተሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ኢንጅነሩ ጠቅሰዋል።

ኢንጅነር ስመኘው እንዳሉት፤ ግድቡ የሚሠራው ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ነው። ይህን ለማከናወን የሚያስችሉ የድንጋይ ወፍጮና የኮንክሪት መሥሪያ ፋብሪካዎች ያስፈልጋሉ። እነዚህን ፋብሪካዎች ለመትከል የዲዛይንና የመሠረት ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ለፋብሪካዎቹ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ግዥ እየተፈጸመ ነው። እየተጓጓዙ ያሉም አሉ። እነዚህ ፋብሪካዎች በሰዓት ሁለት ሺ ቶን ጠጠር ያመር ታሉ። በሰዓት ስምንት መቶ ሜትር ኩብ አርማታ ይሠራሉ።
ለግድቡ ግንባታ የሚውሉ ከባድ መሣሪያዎችም ከውጭ ሲገቡ የመዘግየት ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ በመንግሥት በኩል የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት በአፋጣኝ ወደ ግንባታው ቦታ እየተጓጓዙ እንደሆነ ነግረውናል።

በሌላ በኩልም የፕሮጀክቱ አካል የሆነ የውስጥ ለውስጥ መንገድ በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ግድቡ በሚሞላበት ጊዜ በውሃ የሚሸፍነው ነባሩን መንገድ አቅጣጫ በመቀየር 123 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ነው የገለጹት። በተያያዘም የፕሮጀክቱን ታችኛውንና ላይኛውን አካል ማገናኘት የሚችል 250 ሜትር ያህል ርዝመት ያለው አዲስ ድልድይ እየተሠራ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት የዚህ ድልድይ ሥራም 70 በመቶ ተጠናቋል ብለዋል። ድልድዩም ከኃይል ማመንጫው ግንባታ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን ይረዳል ነው ያሉት።
የሠራተኞች መኖሪያ ቤትም በምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተገነባ ነው። እስከአሁን አንድ ሺ 600 ሠራተኞችን ማስተናገድ የሚችል መኖሪያ ቤት ተገንብቷል። ለግድቡ ግንባታ የሚውሉ መሣሪያዎች የሚጠገኑበት ቤቶች፣ ጋራዦች፣ መጋዘኖች የምግብ ቤቶች፣ ቤተ -ሙከራዎችና የመሳሰሉት እየተሰሩ መሆናቸውንም ኢንጅነር ስመኘው ገልጸውልናል።

በአሁኑ ጊዜ አንድ ሺ 600 ሠራተኞች በግድቡ ግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከእነዚህ ሠራተኞች ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጎች ከ85 አይበልጡም ተብሏል። ይህም ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የላቀ ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
የግድቡ ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ ዋናው የሥራ ተቋራጭ የጣሊያኑ ሣሊኒና ንዑስ ተቋራጩ የኢፌዴሪ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚቀጥሯቸውን የቢሮ ሠራተኞች ሳይጨምር 12ሺ ሠራተኞች በግንባታው ላይ ይሳተፋሉ። እነዚህን ሠራተኞች በሂደት ለመቅጠርም በየክልሉ ሠራተኛ መቅጠሪያ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። ይህም የሀገር ውስጥ አቅም ከመገንባትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ይላሉ ኢንጅነር ስመኘው።

የመንግሥት አቋም ወደፊት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መገንባት መቻል ነው። ከዚህ አኳያም የኃይድሮና ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎችን በንዑስ ተቋራጭነት የኢፌዴሪ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እንዲሰራው ተደርጓል። የሲቪል ሥራውን የጣሊያኑ ሳሊኒ የሥራ ተቋራጭ ኩባንያ እያከናወነ ይገኛል።

እንደ ኢንጂነር ስመኘው አገላለጽ በተቻለ አቅም ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት ጊዜ፣ ጥራትና በጀት ለማጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል። የፕሮጀክት ግንባታ ሂደትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፋጠነ ነው። እስከአሁንም መሣሪያዎችንና የሰው ኃይሉን በማደራጀት በኩል አመርቂ ሥራ ተሰርቷል። ይህም አፈጻጸሙ በጥሩ ሁኔታ እንዲገኝ አድርጓል።
ኢንጅነር ስመኘው ግንባታውን ከማፋጠንና በግድቡ ዙሪያ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ዘንድ የተንፀባረቁትን አሉታዊ አስተሳሰቦችን ከመቀየር አኳያ የተሰራው ስራም ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

እስከአሁን ባለው የሥራ ሂደትም የገጠመ ችግር አለመኖሩን ነግረውናል። በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ሕዝቡ እያሳየ ያለው መነሳሳት እየተቀዛቀዘ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ምን አስተያየት አለዎት? የእኛ ጥያቄ ነበር። ኢንጅነር ስመኘውም «የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር ጀምሮ ትልቅ ሕዝባዊ መነሳሳት ታይቷል። መገናኛ ብዙኃንም ለጉዳዩ ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ታላቅ ሀገር ብዙ ወቅታዊ ጉዳዮች አሏት። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ቀንሶ ሊሆን ይችላል። የሕዝቡ መነሳሳት ግን አሁንም ይበልጥ የጨመረበት እንጂ የቀነሰበት ሁኔታ የለም። አሁንም ድረስ ቢሮ እየመጡ ወደ ቦታው ሄደው ለመሥራት ፍቃደኝነታቸውን የሚገልጹ በርካታ ዜጐች ናቸው ብለዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከመሬት ወደላይ 145 ሜትር ከፍታ ሲኖረው አንድ ሺ 780 ሜትር የጐን ርዝመት ይኖረዋል። ይህ ግድብ ከ63 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ የመያዝ አቅም አለው። ግድቡን በሥራ ተቋራጭነት የሚያከናውነው መሠረቱን ጣሊያን ሀገር ያደርገው ሳሊኒ ነው። ሳሊኒ በኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ባሻገር የተለያዩ የኤሌክትሪክ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ገንብቷል። በዋናነት 420 ሜጋዋት የሚያመነጨውን ግልገል ጊቤ ሁለትን እና 460 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ጣና በለስን መጥቀስ ይቻላል። ግልገል ጊቢ ሦስተኛንም እየገነባ ይገኛል። ይህ ሥራ ተቋራጭ በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ ሀገሮች 20 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን እንደገነባ መረጃዎችእንደሚያሳዩ አዘ ዘግቧል።