የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አካላት ሁለንተናዊ እድገቱን ለማስቀጠል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል-አቶ አዲሱ ለገሠ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 16/2004 (ዋኢማ) – የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አካላት በአገሪቱ የተጀመረውን ሁለንተናዊ እድገት ለማስቀጠል ለኅብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው የኢህአዴግ የሥልጠና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አሳሰቡ፡፡

ሥልጠናውን የተከታተሉ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አካላት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚረባረቡ ገልጸዋል፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ለገሠ ለአካላቱ ባለፉት ሁለት ወራት የተሰጠው ሥልጠና ዛሬ ሲጠናቀቅ እንዳስገነዘቡት አካላቱ የሕዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ደረጃ ለማድረስ መሥራት ይገባዋቸዋል።

በዚህም ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገውን ጥረት ማገዝና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ትክክለኛና ተገቢ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሦስት ዓመት ተኩል የቀረውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት አመራሩና ኅብረተሰቡ በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት እንዳለባቸውም አቶ አዲሱ አሳስበዋል፡፡

ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎችና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጡት ከፍተኛ አመራር አባላት አቶ ደሳለኝ ታየ፣ወይዘሮ ሳኢዳ ከድርና አቶ ተስፋየ ሞገስ እንደገለጹት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸውን እውቀትና ጉልበት በማስተባበር ማንኛውንም መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ አረጋግጠዋል፡፡

በአገሪቱ የሚታዮትን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የጠባብነትና የመሳሰሉትን ችግሮች እንዲወገዱ ለማስቻል አገራዊና ወገናዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

ሰልጣኞቹ ባወጡት ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ እንዳስታወቁት በአገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቀጣይነትና የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።