ጠ/ሚ መለስ አልሸባብን መደገፍ አለም አቀፍ ህግጋትን ከመጣስ ባለፈ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች ላይ ወንጀል መፈፀም ነው አሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2004 (ዋኢማ) – ጠቅላይ ሚስትር መለስ ዜናዊ የሶማሊያ ቀውስ መነሻ የፖለቲካ ቀውስ ነው ብለዋል ለለንደን የሶማሊያ አለም አቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር፡፡

የዚህ ቀውስ መፍትሄ ያለውም በፖለቲካዊ ሂደት ነው ያሉት አቶ መለስ በተለይ እራሳቸው ሶማሊያዊያኑ በቅርበት መነጋገራቸው ያለውን ፋይዳ በጋሮዌ 1 እና 2 ጉባዔዎች መመልከት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በሶማሊያ መረጋጋት እንዲሰፍን የአፍሪካ ሀገራት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸውን ለጉባኤው ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

አልሸባብን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መደገፍ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔዎችና አለም አቀፍ ህግጋትን መጣስ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች መልካም ህይወት ላይ ጥቃት መሰንዘር መሆኑን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘበው ይገባልም ነው ያሉት አቶ መለስ፡፡

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ወታደሮችና የኢትዮጵያ ሰራዊት አልሸባብን በባይ እና ቦኮ አካባቢ ድል በማድረግ ባይዶዋን ነፃ አውጥተዋል፡፡

ባይዶዋ ለአልሸባብ የምልመላና የገንዘብ ማዕከል ስለነበር ድሉ በፀረ ሽብር እንቅስቃሴው ትልቅ ውጤት ይኖረዋልም ብለዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ለጥምር ሰራዊቱ የሰጡት ድጋፍና ባይዶዋ ነፃ ስትወጣ በ10 ሺዎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን መግለፃቸው ሶማሊያውያን የአልሸባብ በደል ምን ያህል እንዳስመረራቸው የሚያስረግጥ ነው፡፡

ሰላም አስከባሪው አሚሶም በሞቃዲሾ፣ ኬኒያና፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከሶማሊያ ወንድሞቻቸው ጋር ተሰልፈው ያስመዘገቡት ውጤት አፍሪካውያንና የቀጠናው ሀገራት ሶማሊያ አልሸባብን ድል በማድረግ ወደ መረጋጋት እንድትመጣ ያላቸውን ድጋፍና እየከፈሉ ያለውን መስዋዕትነት የሚያሳይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በሱማሊያ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም እየያዘ መምጣቱ በወቅቱ ያለው አንፃራዊ መረጋጋትን ለማጠናከር አጋዥ ነው ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪን ለማጠናከር በሙሉ ድምፁ ውሳኔ ማስተላለፉ ይህን የሚያንፀባርቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአልቃኢዳና ከሽብር ጋር በተያያዘ ያለው አቋም ወጥ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የለንደኑ አለም አቀፍ የሶማሊያ ጉባኤ በዋናነት ሰብአዊ ድጋፍን ለማስፋፋት የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪን ለማጠናከርና የተደራጀ አለም አቀፍ ድጋፍ ለሶማሊያዊያን አንድነት ለመስጠት በመስማማት ተጠናቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በጉባዔው ላይ ተሳትፈው የካቲት 16/2004 ዓ.ም ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸውን ኢሬቴድ ዘግቧል፡፡