የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቱን በአርብቶ አደረች አካባቢ ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ ተጀምሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22 ቀን 2004 (ዋኢማ) – ” እንደ አርሶ አደሮች ሁሉ አርብቶ አደሩንም የሃብት ባለቤት ለማድረግ በአፋርና በሱማሊ ክልሎች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ ተጀምሯል”። ግብርና ሚኒስቴር።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ መሰረታዊ ዓላማ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ ሀገራችንን ከተመፅዋችነት የሚያላቀቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ የዳበረ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ነው።

ፖሊሲው አራት መሰረታዊ ገፅታዎች ያሉት ሲሆን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ፣ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ አገራችንን ከተመፅዋችነት ማላቀቅና የዳበረ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት የሚሉት ናቸው።
ከኢኮኖሚ ፖሊሲዉ አራት ገፅታዎች አንዱና ለስኬታማነቱም መሰረት የሚሆነው ፈጣን፣ የማይቆራረጥና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ ነው።

ፖሊሲው ለልማት ከሚያስፈልጉት ግብአቶች መካከል ካፒታል፣ ጉልበትና መሬት ዋነኞቹ መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ስትጀምር ይህ ነው የሚባል ካፒታል በተለይም ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያልነበራት ቢሆንም እጅግ ሰፊ የሆነ የሰው ጉልበትና መሬት በመጠቀም ግን ብዙዎችን ያስደመመ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታና የምዕተ አመቱ የልማት ግቦች ማሳኪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እርእስቱ ይርዳ እንደሚሉት እጥረት ያለበትን ካፒታል በላቀ ቁጠባ፣ እጥረት የማይታይበት ጉልበት ደግሞ በስፋት በመጠቀም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የተመሰረተ የልማት ስትራተጂ ተግባራዊ በማድረግ ባለፉት ሰባት አመታት አመርቂ ውጤት ተመዝግቦበታል።

የኢኮኖሚ ፖሊሲው ሰፊውን ህዝብ በተለይ ደግሞ አርሶ አደሩ ህብረተሰብ የሃብት ባለቤት አድርጎል፣ በሚሊዮን የሚገመት ካፒታል የሚቆጥሩ አርሶ አደሮች አፍርቷል፣ ቆርቆ ቤቶችን መገንባት፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የመጠቀም

ፍላጎት አድጓል ። ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን በስፋትና በጥራት ወደሚያቀርቡበት ደረጃ እየተሸጋገሩም እንደሚገኙባቸዉ ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩ ማህበረሰብ ላይ አበረታች ዕድገት ቢታይም አርብቶ አደሩ ግን በሚፈለገው መጠን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ አልሆነም እንደሚኒስትር ዲኤታው ገለፃ።

አርብቶ አደሩ ህዝብ በተለይ የሶማሊና የአፋር ህዝብ አብዛኛው በሃገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በተበታተነ ሁኔታ የሚኖር መሆኑን፣ የኑሮ መሰረቱ በእንሰሳት ሃብት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ ለእንሰሳት መኖና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሰ የሚኖር፣ አካባቢው ለተደጋጋሚ የዝናብ እጥረትና የተዛባ ስርጭት የተጋለጠና በድርቅ የሚጠቃ ነው።

በዚህ ምክንያት ለውሃ እጥረት የተጋለጡ፣ ድርቅን ተከትለው ለሚመጡ ወባና ውሃ ወለድ በሽታዎች የተጋለጡ፣ በውሃና በመኖ እጥረት የኑሮ መሰረቱ የሆኑት የእንሰሳት ሃብቱ የሚረግፍበት፣ እንሰሳቱን ተከትሎ ከቦታ ቦታ በሚያደርገው ረዥም ጉዞ የስራ ጊዜው የሚባክንበትና የዳበረ የስራ ልምድ የሌለው መሆኑ ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገበት አቶ እርስቱ ይናገራሉ።

የተጠቀሱት ችግሮች በአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ልማት ላይ የተደቀኑ ጋሬጣዎች ቢሆኑም አርብቶ አደሮቹ እንደ አርሶ አደሮቹ ሁሉ የልማቱ ተሳታፊዎችና ተጠቃሚዎች የሚያደርጉ በርካታ መልካም እድሎች መኖራቸው ደግሞ እዉነት ነዉ ።

በአፋርና በሶማሊ ክልሎች ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ነገር ግን ጥቅም ላይ ያልዋሉ ታላላቅ ወንዞች መኖራቸው፣ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት የሚገኙባቸው አካባቢዎች መሆናቸው፣ በሃገሪቷ ደጋና ወይናደጋ የሚዘንበው ዝናብ የነዚህ ክልሎች ከርሰ ምድር ውሃ የሚያበለፅግ መሆኑንና ለእርሻና ለእንሰሳት መኖ ልማት ተስማሚ የሆነ ከፍተኛ ለም መሬት ባለቤት መሆናቸው ብሩህ ተስፋ ፈንጣቂ ነው።

ይህ ሁሉ ዕድል እያለ ጥቅም ላይ ሳይውል በመቆየቱ አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በድህነት እየማቀቀ መቆየቱን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት በአምስት ዓመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለአርብቶ አደሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከመንደር ማሰባሰቡ ስራ ጋር በማዋሃድ በርካታ ተግባራት ማከናወን ጀምሯል።

የአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሶማሊ ክልል አምስት፣ በአፋር ከልል ደግሞ ሶስት የልማት ቀጠናዎች ተሰይመዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እርእስቱ ይርዳ እንደሚሉት በሶማሊ ክልል የተለዩ አምስት የልማት ቀጠናዎች የሽንሌ ዞን፣ ጎዴና ከፊል አፍዴር የያዘው የሸበሌ ልማት ቀጠና፣ አፍዴርና ሊበን ዞኖችን ያካተተው የገናሌ ዳዋ የልማት ቀጠና፣ ጂጂጋ ደገሃቡርና ቀብሪደሃር ያካተተው ፋፈም ጀረር የልማት ቀጠናና ዋርደርና ከፊል ጂጂጋ ያጠቃለለው የምስራቅ ሶማሊ የልማት ቀጠና ተብሎ ተለይቷል።

በአፋር ክልል የተለዩ የልማት ቀጠናዎች ደግሞ መካከለኛውና ታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ የሚያጠቃልለው የደቡብ አፋር የልማት ቀጠና፣ ምዕራባዊ ደጋማ የደናክል ተፋሰስ አካባቢዎችን ያካተተው ሰሜናዊ ምዕራብ አፋር የልማት ቀጠናና ከምስራቃዊ ደናክል እስከ ዳሎል ያለው ሰሜን ምስራቅ አፋር የልማት ቀጠና ተብለው የተሰየሙ ናቸው።

የልማት ስራውን በተቀናጀ መልኩ ለመምራት የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠሩን የገለጡት ሚኒስትር ዲኤታው በፌዴራል ደረጃ አንድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ በሶማሊ ክልል አራትና በአፋር ክልል ሁለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተከፍተው በባለሙዎች እንዲጠናከሩ ተደርጓል።

በሁለት ክልሎች በዘንድሮ ዓመት ለሚከናወኑ ልማታዊ ስራዎች አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበ ሲሆን ዋና ዋና ተግባራቱም ውሃን መሰረት ያደረገ የመስኖ ልማት፣ የግጦሽ መሬት ማዘጋጀትና ማልማት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ስድሳ ሺህ የሚጠጉ አርብቶ አደሮችን በመንደር ማሰባሰብ ነው ተብሏል።

በዘንድሮ ዓመት በአፋር ሰላሳ አምስት ሺህ፣ በሶማሊ ሃያ አራት ሺህ አርብቶ አደሮች በመንደር እንዲሰባሰብ የሚያደርግ ቢሆንም ስራው ግን በቀጣዩ ዓመታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጧል።

ዘንድሮ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከልም በሶማሊ አራት ሺህ ሔክታር፣ በአፋር ደግሞ ሁለት ሺህ ሔክታር መሬት የሚያለማ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ይገኝበታል።

የሶማሊ ክልል የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ማሳኪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሲኒየር ጂኦሎጂስት አቶ ሃምዲ አህመድ እንደገለጡት መንግስት ለአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት አምስት መቶ ዘመናዊ የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች ተገዝቶ ለአርብቶ አደሩ መከፋፈሉንና ዘንድሮም አንድ ሺህ ሰባት መቶ ፓምፖች ተገዝተው ወደ ክልል መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች አራት ሺህ አርብቶ አደሮች በፍቃደኝነት በመንደር እንዲሰባሰቡ የማሳመን ስራ መካሔዱንም አስረድተዋል።

በአፋር ክልል የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ማሳኪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የእንሰሳት እርባታና የተፈጥሮ ግጦሽ መሬት አያያዝ ባለሙያ አቶ መስፍን ጌታነህ በበኩላቸው በክልሉ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ለማሳካት ሁሉም አካላት ርብርብ ጀምረዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ሰላሳ አምስት ሺህ አርብቶ አደሮች በመንደር ለማሰባሰብ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የገለጡት ባለሙያው አስራ ስምንት ሺህ አርብቶ አደሮች በመንደር የሚሰባሰቡት እየተከናወነ ካለው የስኳር ልማት ፕሮጀክት ጋር በማስተሳሰር መሆኑን ገልጠዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉም አካላት እንደሚሉት እንደ አርሶአደሩ ሁሉ አርብቶ አደሩ ማህበረሰብም በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት የልማቱ ዋነኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ኢዜአ ዘግቧል።