ፎረሙ ለኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2004 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም የአገሪቱን ባለሃብቶች ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አዘጋጅ ኮሚቴው ገለጸ፡፡

አዘጋጅ ኮሚቴው ከባለሃብቶች፣  ከንግዱ ማህበረሰብና   የዝግጅቱን ሂደት ለመገምገም ከፎረሙ ከተላኩ ተወካዮች ጋር ትናንት በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው የሚካሄደው ኮንፈረንስ በዓለም ደረጃ ከሚካሄዱት ታላላቅ የኢኮኖሚ ኮምፈረንሶች አንዱ በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡

ፎረሙ በአገሪቱ ያለውን ኢንቬስትመንት ለማስፋትና ባለሃብቶች በዓለም ኢኮኖሚ ተጽእኖ ከሚያደርሱ አካላት ጋር ለመተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

በዚሁ መድረክ የተገኙት የስዊዝ ዌስት ኢንጂኔሪንግ  ስራ አስፈጻሚ  አቶ ቴወድሮስ አሸናፊ እንደገለጹት  ባለሃብቱ ይህንን ልዩ አጋጣሚ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

አቶ አሸናፊ አያይዘውም “ፎረሙ ካፒታልንና ኢንቬስትመንትን ከመሳብ አንጻር፣ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ከማሳየትና በአገሪቱ ያሉ ዘርፈብዙ የኢንቬስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ የአገራችን ባለሃብቶች ይህንን ባግባቡ ይጠቀሙበታል የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡”

አቶ ቴዎድሮስ በመቀጠልም ኮንፈረንሱ የተቀረው ዓለም ስለኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ ግምት ለማስተካከልና በአገሪቱ እየታየ ያለውን የኢኮኖሚ ለውጥ ለማስረዳት ያስችላል ብለዋል፡፡

የኤርነስ ኤንድ ያንግ የምስራቅ አፍሪካ ማኔጅንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው አዘጋጅ ከሞቴው ከንግዱ  ማህበረሰቡ ጋር ያደረገው ውይይት ጥሩ ግንዛቤ ያስጨበጠና ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አቶ ዘመዴነህ አያይዘውም የኮንፈረንሱን ፋይዳ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማስረጽ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው ኮንፈረንሱ የአገራችንን ባለሃብቶች ከዓለሙ የንግድ ማህበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡