ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን ፈለግ በመከተል ድሕነትን ማሸነፍ ይገባዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2004 (ዋኢማ) – ወጣቱ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹን ፈለገ በመከተል ድሕነትን ማሸነፍ እንደሚገባው አፈ ጉበዔው ገለጹ፡፡ የአድዋ ድል 116ኛው ዓመት መታሰቢያ በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ በድምቀት ተከብሯል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈባኤ አባዱላ ገመዳ በምኒልክ አደባባይ ስር የአበባ ጉንጉን ባስቀመጡበት ወቅት እንዳሉት ጥንት አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ጣሊያንን እንዳሸነፉት ሁሉ ወጣቱ ትውልድ ደግሞ ጠንክሮ በመስራት ከድሕነት ሊወጣ ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን ለማልማት የሕይወትና ሌሎች መስዋእትነትን የሚጠይቅ ሳይሆን እድገትን በማፋጠንና አሁን ባለው የተመቻቸ ሁኔታ በመጠቀም ታሪክ መሰራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

ወጣቱ ጥንት አባቶቻችን አድዋ ላይ ያስመዘገቡትን ድል ከመዘከር ባሻገር በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ውጤትም ተከታታይ እንዲሆን ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሐን አስታጥቄ አባተ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ አድዋ ላይ ግፈኛውንና ወራሪውን የጠላት ድል እንደመታው ሁሉ የአሁኑ ትውልድም በድህነት ላይ አርበኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ካነጋገርናቸው አባት አርበኞች መካከል አቶ አበበ አስረሳህኝ እንደተናገሩት በአሉ በየአመቱ መከበሩ ለአለም በተለይም ለአፍሪካ ሕዝብ ኩራት ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ትውልዱ ይህንን ታሪክ በመድገምና በቴክናሎጂ፣ በእድገት፣ በልማትና የኢኮኖሚ እድገቱን በማፋጠን ረገድ ጠንክሮ በመስራት ሊደግመው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት ወይዘሮ ደሞዝ ምህረቱ በድህነት ላይ አጃችንን በማንሳት የአባቶቻችንን አኩሪ ገድል በመድገም ኢትዮጵያን መለወጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በአገሪቷ እድገት መኖሩ የማይካድ ነው ስለዚህም ትውልዱ ጅማሬው እንዳይሰናከል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ሌው አስተያየት ሰጪ ወጣት ሰለሞን አዲሱ እንዳለው ድሉ ምንም እንኳን አባቶቻችን ጣሊያንን ድል በማድረግ ቢያቆዩልንም አሁን ከኛ የሚጠበቀው ደግሞ አገሪቱን ካደጉ አገራት ተርታ ማሰለፍ ነው ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡