የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ከፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ጋር ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2004 (ዋኢማ) – በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሰለኝ የሚመራ የኢህአዴግ ከፍተኛ የአመራር ቡድን ከደቡብ አፍሪካ የናሽናል ኮንግረስ መሪና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት    ጃኮብ ዙማ ጋር ተገናኝቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየቱ ተገለጸ፡፡

የኢህአዴግ ጽ/ቤት ለዋልታ በላከው መግለጫ እንደገለጸው ውይይቱ ሁለቱ ፓርቲዎች ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማጠናከር፣ የአፍሪካ ተራማጅ ፓርቲዎች መድረክን፣  በፓርቲዎቹ መካከል የተጀመረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ የመንግስት ለመንግስትና የሀዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከርና የአፍሪካን ችግር ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡

በውይይቱ  ላይ የሀገሪቱ ም/ፕሬዚዳንት ሚስተር ካሊማ ሞትለንቴ፣ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሚስስ ባሌካ መቤቴ፣ የፓርቲው ዋና ፀሀፊ ሚስተር ጉዌድ ማንታሼ እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት መገኘታቸውንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡

የኢህአዴግ ም/ሊቀ መንበርና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ  እና የኢህአዴግ ም/ቤት ፅ/ቤት ሃላፊና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሬድዋን ሁሴን በአፍሪካ  ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ  ሃላፊዎች በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት ነበር በደቡብ አፍሪካ ከየካቲት 18 እስከ የካቲት 21/2004ዓ.ም ለአራት ቀናት የቆየ የስራ ጉብኝት ያካሄዱት፡፡

የልኡካን ቡድኑ በደቡብ አፍሪካ ቆይታው በጆሃንስበር የሚገኘውን ፍሪደም ፓርክ እና በስዌቶ ከተማ የማንዴላ የቀድሞ መኖሪያ ቤትና የአካባቢው ተማሪዎች ትግል ያካሄዱበትን ት/ቤቶችና ፀረ-አፓርታይድ ትግሉን የሚያሳዩ ሙዚየሞችን መጎብኘቱንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡