ኢትዮጵያ የዩኔስኮ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆና ተመረጠች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2004 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባለ ሆና መመረጧን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት ምንም እንኳን የአስፈጻሚ አባልነት ተራዋን የተወጣች ቢሆንም እንደገና ለውድድር ቀርባ በመመረጧ የቦርድ ስራ አስፈጻሚ አባል ሆና እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዩኔስኮ አጠቃላይ ኮነፈረንስ የተመረጠችው አገሪቱ በትምህርት ዘርፍ እያደረገች ያለውን ጥረትና የሚታየው ውጤትን መሰረት ያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የህዝቡ ሙሉ ተሳትፎና የመንግስት ቁርጠኝነት ተጣምረው በአገራችን የትምህርት ስርዓቱን ተደራሽ የማድረግና ጥራቱን የማስጠበቅ ስራ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የምዕተ ዓመቱን የተባበሩት መንግስታት የልማት ግቦች ለማሳካት ከተለያዩ ዓለምአቀፍና አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ከሌሎች የልማት አጋሮቿ የሚደረግላትን ድጋፍ በመጠቀምና የራሷን ሙሉ አቅም አሟጣ በመጠቀም ለስኬት እየሰራች መሆኑንም አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም በአገራችን ያለውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ትምህርትን የጥራት ደረጃ ለመጠበቅና በተገቢው መንገድ ለማስፋት በተለይ ከዩኔስኮ ጋር የትብብር ስምምነት ተፈጥሮ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡