የአሜሪካ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 9/2005 (ዋኢማ) – የአሜሪካ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋለነዋያቸውን እንዲያፈሱ መንግስት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ከሰላም ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደገለጹት የአሜሪካ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የኢንቨስተመንት መስክ እንዲሰማሩ መንግስት ፍላጎት አለው፡፡

ኢትዮጵያና አሜሪካ ጥሩና የቆየ ወዳጅነት አላቸው ያሉት አምባሳደር ብርሃነ ይህ ወዳጅነት ሽብርተኝነትን በመዋጋትና ለአፍሪካ ሰላም መስፈን በጋራ በመስራት እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል አሁን ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በኢንቨስትመንት መስክም እንዲደገም ኢትዮጵያ ጠንካራ ፍላጎት እንዳለት አምባሳደር ብርሃነ ተናግረዋል፡፡

አሁን ስላለው የአገረቱ ወቅታዊ ሁኔታም ሲናገሩ ኢትዮጵያ በፈጣንና በአስገራሚ የእድገት ጎዳና ላይ እደምትገኝና የድህነት ጣራም ከ7 ዓመት በፊት 53 በመቶ የነበረው እኤአ በ2010 ወደ 29 በመቶ ሊወርድ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

አሁን ያለውን በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቀጠይነት ለማረጋገጥም መንግስት ለመሰረተ ልማት መስፋፋት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፤ በዚህም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 64ሺህ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ  እንደሚገነባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ አሁን ያላትን 2ሺህ 200 ሜጋ ዋት የሀይል አቅርቦት በሚቀጥሉት ሀለት ዓመታት ውስጥ ወደ 10 ሺህ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደር ብርሀነ የስኳር አቅርቦትንም አሁን ካለበት 330ሺህ ቶን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ወደ 2 ነጥብ 2 ቶን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

ትምህርትን በተመለከተም በአሁኑ ጊዜ 105 ዩኒቨርሲቲዎች በመላው አገሪቱ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 31ዱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን መሆናቸውን ታናግረዋል፡፡ ከ20 ሚሊየን በላይ ህጻናትም ትህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ብርሃነ በመጨረሻም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡