በስኳር ህመም ሳቢያ የሚከሰተውን የዓይን ብርሃን ችግር ለመከላከል የሚያስችል ስልጠና እየተካሄደ ነው

 

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2004/ዋኢማ/ – በስኳር ህመም ሳቢያ የሚከሰተውን የዓይን ችግር አስቀድሞ ለመከላከል በዓይን ህክምና ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አቅም ሊያሳድግ የሚችል ስልጠና በመካሄድ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር አስታወቀ።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ፋካልቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሪሀብሊቴሽን ሴንተር የተዘጋጀውን የአምስት ቀናት የህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ሲከፍቱ እንደገለፁት፤ ከስኳር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የዓይን ብርሃን ማጣት ችግር በቀላሉ ለማዳን ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ይገባል።

ከስኳር ህመምተኞች 40 በመቶ የሚሆኑት ለዓይን ብርሃን ማጣት ችግር ይጋለጣሉ ያሉት ዶክተር አህመድ፤ ችግሩን ግን  ክትትል ከተደረገ በቀላሉ ማዳን እንደሚቻል ተናግረዋል።

የስኳር በሽታ ለረዥም ጊዜ ቁጥጥር ሳይደረግለት ሲቀር የአይን አንዱ አካል የሆነውን ሬቲና አካባቢ ያሉትን ጥቃቅን የደም ስሮችን በማወክ የአይን ብርሃንን ሊያጠፋ እንደሚችል ጠቁመው፤ ችግሩ በወቅቱ ታውቆ ቁጥጥር ከተደረገበት ግን ሊድን የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ማህበሩ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከወርልድ ዲያቤትስ ፋውንዴሽን ከተባለ ድርጅት ስምንት ሚሊየን ብር የሚገመት ፓስካል የተባለ የህክምና መሳሪያና የዓይን አካል የሆነውን ሬቲና በፎቶግራፍ ለማንሳት የሚያስችሉ አራት ዘመናዊ የሬቲና ፎቶግራፍ ማንሻ ዲጂታል ካሜራዎችን በእርዳታ መገኘቱን ተናግረዋል።

የተገኙትንም መሳሪያዎች ለጅማ፣ ጎንደር፣ ሀዋሳና መቀሌ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ለማስረከብ መታቀዱን ገልፀው፤ በዛሬው ዕለትም ከአራቱም ሆስፒታሎችና ከራስ ደስታ፣ ሚኒሊክና ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች የተውጣጡ 40 የዓይን ህክምና የጤና ባለሙያዎች ስለ ማሽኑ አጠቃቀም አጠቃላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን  ገልፀዋል።

ለሰልጣኞቹም ከእንግሊዝ በርሊንግሀም የመጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና አየሰጧቸው መሆኑን ገልፀው፤ ሰልጣኞቹም ስለማሽኑ በተግባርና በንድፍ ሀሳብ ደረጃ በተገቢው መንገድ እንዲያውቁት የማስቻል ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ቀደም ባሉት አመታትም ሁለት የሬቲና ፎቶግራፍ ማንሻ  ካሜራ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት ላይ መዋሉን የገለፁት ዶክተር አህመድ፤ አሁን በእርዳታ የተገኙት አራቱን ለየሆስፒታሎቹ በማከፋፈል የችግሩን አሳሳቢነት በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

የበርሊንግሀም ቡድን ከሶስት ወር በኋላ ተመልሰው በመምጣት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትና ሰፋ ያለ ትምህርት ለመስጠት ማቀዳቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።