የግል የግንባታ ሥራ ተቋራጮች በመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ሀዋሳ ጥቅምት 23/2004/ ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል የሚገኙ የግል የግንባታ ሥራ ተቋራጮች በልማት ሥራዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ የዲዛይንና የግንባታ ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለፀ።

ባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ማርቆስ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የግል የግንባታ ሥራ ተቋራጮች በመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች ያላቸው ሚና እያደገ መጥቷል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አሥር ፍቃድ ያላቸው 302 የግንባታ ሥራ ተቋራጮች በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ተቋራጮቹ ከተለያዩ የክልሉ አስፈጻሚ ቢሮዎች ጋር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የግንባታ ውሎችን በመገንባት 563 የግንባታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ተቋራጮቹ በአብዛኛው በመንገድ፣ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስራዎች ላይ እተየሳተፉ መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ እያሱ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ክልሉ ያለውን ውስን ሀብት ሳያባክን ፕሮጀክቶቹን በቁጠባ በጥራትና  በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲከናወኑ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶችንና አሠራሮችን ዘርግቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በተለይም በግንባታ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ፈጥኖ ለመለየት፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመቀየስና መረጃዎችን ለመለዋወጥ የክልሉ መንግሥት፣ የሥራ ተቋራጮች፣  የግንባታ አማካሪዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ቋሚ የጋራ የውይይት ፎረም መኖሩን አመልክተዋል።

ተቋራጮቹ እያከናወኑ የሚገኙት የልማት ፕሮጀክቶች በክልሉ የመሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ከሚኖራቸው ፋይዳ በተጨማሪ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለክልሉ ዓመታዊ ምጣኔያዊ የምርት ዕድገት የራሳቸውን ድርሻ እያበረከቱ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ መጠቆማቸውን ዋልታ ኢንፎርማሽን ማዕከል ዘግቧል።