ክልሉ ድህነትን ሊቀርፉ የሚችሉ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት መስጠቱን አስታወቀ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 23/2004/ዋኢማ/ – በዘንድሮው የበጀት ዓመት ድህነትን ማዕከል ላደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሀረጋዊ ሲማ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የክልሉ መንግሥት በ2004 ዓመተ ምህረት ለልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከመደበው 10 ቢሊዮን 827 ሚሊዮን ብር ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ ድህነት ተኮር ለሆኑ የግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ አነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች ማስፋፊያ፣ ውሃና የመንገድ ፕሮጀክቶች ማከናወኛ የሚውል ነው።

ዘንድሮ በክልሉ ሊካሄዱ ከታቀዱት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ የድህነት ቅነሳ ግቦችን መሠረት ያደረጉ ናቸው ያሉት አቶ ሀረጋዊ በተለይ በበጀት ዓመቱ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን ከማሻሻልና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ በተጨማሪም 18 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ተቋማት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ገልፀዋል።

እንዲሁም 50 የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ 42 የገጠር የመጠጥ ውሃ ተቋማት ቁፋሮ፣ 82 የጤና ጣቢያዎች፣ 48 የገጠር ሆስፒታሎች ግንባታና 575 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ መንገዶች ግንባታዎች  እንደሚካሄዱ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለመጀመር አስፈላጊው መሰናዶ መጠናቀቁን ያመለከቱት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ሥራዎቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ያልተቋረጠ የድጋፍና የክትትል ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

ክልሉ ለድህነት ቀነሳ ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት መስጠቱ በየደረጃው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች አገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ መካሄድ የሚሊኒየም ግቦችን ለማሳካትና የክልሉንና የአገራችንን ኢኮኖሚ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማሸጋገር የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚኖራቸው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ማመልከታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።