ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ፈረንሳይ ሄዱ

አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2004/ዋኢማ/ – ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዛሬ  ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ትናንት ወደ ፈረንሳይ ሄደዋል።

የቱሪስቶች የመዝናኛ ስፍራ በሆነችው ካን የሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

ወቅታዊው የአለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ በተለይም የአውሮፓ ሀገራት ያጋጠማቸው ከፍተኛ የእዳ መጠንና አሉታዊ ውጤቱ፣ የታዳጊ ሀገራትን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት ያሉ አማራጭ ማለትም መንገዶችና በአለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚሉት በስብሰባው የሚተኮርባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ባለፈው አመት ህዳር ላይ በደቡብ ኮሪያ ሴኡል በተካሄደው የአባል ሀገራቱ ስብሰባ ላይ የታዳጊ ሀገራትን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት ያሉ አማራጮችን የሚያጠናና 17 አባላት ያሉት ከፍተኛ የአማካሪ ቡድን መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

ቡድኑም የመጀመሪያ ዙር ሪፖርቱን ባለፈው መስከረም ለተካሄደው የአባል ሀገራቱ ስብሰባ  የቀረበ ሲሆን፤ የመጨረሻ ሪፖርቱም ለመሪዎቹ ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተበሎ ይጠበቃል፡፡

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የቡድኑ ሪፖርት ከመንግስታት በጀት በተጨማሪ ከግሉ ዘርፍ ለመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የሚውለውን ገንዘብ የሚገኝበትን አማራጮች የዳሰሰ ይሆናል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ አካባቢያዊ ተቋማት አማካኝነት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በተቀናጀ መልኩ እንዲካሄዱም ሀሳብ ይዟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲነሱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አሸኛኘት መደረጉን የኢሬቴድ ዘግቧል፡፡