16ኛው ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና አባላዘር በሽታዎች የአፍሪካ ጉባዔ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2004/ዋኢማ/ – በመጪው ህዳር 24 በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 16ኛው ዓለም አቀፍ “የኤችአይቪ/ኤድስና አባላዘር በሽታዎች የአፍሪካ ጉባዔ” ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ዓለም አቀፍ የኤድስና አባላዘር በሽታዎች ጉባዔ በአፍሪካ “አይካሳ” አስታወቀ። ለጉባዔው መሳካትም መላው ህብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የአይካሳ ሰብሳቢ ዶክተር ይገረሙ አበበ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ለጉባዔው መሳካት ከ27 በላይ ብሔራዊ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ስራው በተቀላጠፈ መልኩ እየተካሄደ ነው።

ለጉባዔው የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ጉባዔው የሚካሄድበትን የሚሊኒየም አዳራሽ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማደራጀት ስራ፣ እንግዶች የሚያርፍባቸውን ሆቴሎች የመምረጥና የትራንስፖርት አገልግሎት የማመቻቸት ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ስብሰባው የሚካሄድበት የሚሊኒየም አዳራሽ የተለያዩ ስብሰባዎችን በአንድ ጊዜ ሊያስኬድ በሚያስችል መልኩ የመከፋፈል ስራ ተጠናክሮ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ አዳራሹን ለመከፋፈል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን መንግስት ባደረገው ድጋፍ ከውጪ ማስገባት መቻሉን አስታውቀዋል።

በቀሪው ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም ዝግጅቶቹን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባዔው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአካባቢን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ ዝግጅት እንደተደረገም ዶክተር ይገረሙ ገልፀዋል።

በጉባዔው ላይ ከተለያዩ የአለም ሀገራት የሚመጡ ተመራማሪዎች ጥናቶችንና የጥናት ውጤቶችን የሚያቀርቡ መሆናቸውን ዶክተር ይገረሙ ገልፀዋል።

አምስት ቀናት የሚካሄደው ይኸው ጉባዔ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ በአባላዘር፣ በወባና ቲቢ በሽታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚወያይ መሆኑንም አመልክተዋል።
በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ እንግዶችም በአዘጋጁ ድህረ ገፅ አማካኝነት ምዝገባቸውን እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እስካሁንም አራት ሺ የሚሆኑ ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ጉባዔውን ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው እንግዶች እንደሚመጡ የገለፁት ዶክተር ይገረሙ፤ ህብረተሰቡም የቆየ የኢትዮጵያ ባህል የሆነውን እንግዳ ተቀባይነት በተግባር በማሳየት የበኩሉን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ