ኢንስቲትዩቱ ለእቅድ ተግባራዊነት በጥናትና ምርምር ለመደገፍና ለዓቅም ግንባታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መስጠቱ የሚበረታታ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2004/ዋኢማ/– የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት አለምዓቀፍ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊነት በጥናትና ምርምር ለመደገፍና ለአቅም ግንባታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መስጠቱ በጠንካራ ጎኑ የሚታይ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ የውጭ፣ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳባ የኢንስቲትዩቱን የ2004 ዓ.ም ዕቅድ ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው በእቅዱ ማስቀመጡ ለቋሚው ኮሚቴ ክትትልና ድጋፍ ለመስጠት የሚያግዝ ነው፡፡

በዘንድሮ የበጀት ዓመት እቅድ ከመሠል ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ዝርዝር አቅጣጫ በማስቀመጡ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሰው ሃይልና በቁሳቁስ ተቋሙን ለመገንባት እቅዱ ላይ የተቀመጡ ትኩረት የተሰጣቸው መልካም እንደሆነም አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ ከሌሎች ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች በተሻለ መልኩ እቅድና ሪፖርት በማዘጋጀት ከቋሚ ኮሚቴው ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በጠንካራ ጎኑ የሚታይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ትኩረትና መሻሻል መካተት ይገባቸዋል ካላቸው መካከል በበጀት ዓመቱ ምን ያህል የምርምር ሥራ ለመስራት፣ ዓውደ ጥናቶች መቼና ምንያህል ይካሄዳሉ፣ የድርጊት መርሃ ግብርና የአፈጻጸምና የክትትል አቅጣጫ የእቅዱ አካል ያለመሆናቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በአካባቢጥበቃ፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስና በሴቶች ተሳትፎ የተመለከተ በእቅዱ ላይ የተቀመጠ ባለመኖሩ ቢስተካከል ሲል ቋሚ ኮሚቴው በአስተያየቱ ላይ ጠቁሟል፡፡

የኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ስብዓት ነጋ በበኩላቸው የተቋሙ ዓላማ ኢትዮጵያ ከዓለም ዓቀፍ ማኀበረሰብ ጋር የምታደርገውን ትብብርና የምትመሠርተው ቅንጅት ለማሳካት የሚረዳ ጥናት፣ ምርምርና ሥልጠና ማካሄድ ነው ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች ከቋሚ ኮሚቴው የተለያዩ ¬ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡