አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2004/ ዋኢማ/ -የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፉት 14 ዓመታት ከ79 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመንገድ ግንባታ ማከናወኑን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ባለፉት 14 ዓመታት በመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ያከናወናቸውን ተግባራት እና የመንገድ ዘርፍ ልማት ደረጃ ሦስትን የሚገመግም አውደጥናት ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ባለስልጣኑ ባለፉት ዓመታት ባካሄደው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ያከናወናቸውን ተግባራት በአውደ – ጥናቱ ላይ ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዛይድ ወልደገብርዔል እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የ25 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ግንባታ ተካሄዷል፡፡
በዚህም በመንገዶች ላይ ከፍተኛ መሻሻሎች መታየታቸውንና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አመልክተዋል፡፡
በፕሮግራሙ 765 ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም 530 ፕሮጀክቶች ለአገር ውስጥ ድርጅቶች መሰጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም 35 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የሲቪል ስራዎች ኮንትራት ለአገር ውስጥ ተቋራጮች መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና ድህነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ለመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሙ ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ 71 በመቶው በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፤ ቀሪው ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተገኘ ድጋፍ መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 14 ዓመታት የሀገር በቀል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን የተናገሩት አቶ ድሪባ መንግስት አሁንም አገር በቀል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በቁርጠኝነት ይንቀሳቀሳል ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ የአገሪቱ የመንገድ ዘርፍ ሊደግፉ የሚችሉ አዳዲስ ኮንትራክተሮችንና አማካሪዎችን ለማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡
ለመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሙ ባለፉት 14 ዓመታት የዓለም ባንክ ከአጠቃላይ ወጪው 10 በመቶውን መሸፈኑን ጠቁመው፤ ይህም ባንኩን ከኢትዮጵያ መንግስትና ከመንገድ ፈንድ ቀጥሎ ሦስተኛው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሰጪ አድርጐታል ብለዋል፡፡
ለፕሮግራሙ መሣካት ከመንግስት ባሻገር አስተዋጽኦ ያደረጉት የብዙዮችና የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ያበረከቱ የልማት ድርጅቶችን ማመስገናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።