የአሜሪካ የሕጻናት አድን ድርጅት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ 70 ሚሊየን ዶላር መደበ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 22/ 2004/ ዋኢማ/– በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ለሚካሄደው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስፈጸሚያ 70 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን የአሜሪካ የሕፃናት አድን ድርጅት አስታወቀ::

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ዶክተር አክሲል ዋይዘር የፕሮግራሙን በይፋ መጀመር ለማስተዋወቅ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተጀመረው የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ፕሮግራሙ በወረዳዎቹ የተከሰቱ የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል::

የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ  የሚካሄደው በሶማሌ ክልል ፊልቱ፣ ዶሎ ባይ፣ ዶሎ ኦዶ፣ ቦሬና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን አሮሬ ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል::

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሚካሄደው በዚሁ ፕሮግራም በወረዳዎቹ የሚገኙ ከ112 ሺ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል::

ነዋሪዎቹ የተረጂነት ስሜት እንዳያዳብሩ ለማድረግ ከምግብ አቅርቦቱ ጎን ለጎን የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል::

በፌዴራል የግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ የሚካሄድባቸው ወረዳዎች ዝናብ አጠር በመሆናቸው ለተደጋጋሚ የምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን አስረድተዋል::

የፕሮግራሙ መካሄድ የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል የገለጹት    ዳይሬክተሩ ለፕሮግራሙ ስኬት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል::