ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የፓን አፍሪካ የቴክኒክ ማህበር የልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/2004/ – ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከፓን አፍሪካ የቴክኒክ ማኅበር መስራች ከሆኑት ፍሬድሪክ ያው ዴቪስ ከሚመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ በውይይቱ ላይ ማኅበሩ ያለውን እውቀት በአፍሪካ ውስጥ ለማካፈል የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸው፤ ይህንን ግንኙነት ለማጠናከርና ለማሳደግ ጥረት መደረግ እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡

ማኅበሩ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በመከላከሉ ረገድ ትግል ያደረገውን ስመጥር አፍሪካ አሜሪካዊ የኮሎኔል ጆንሰን ብራውን ጆንሰን የህይወት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ለፕሬዚዳንት ግርማ አበርክቷል፡፡

ፕሬዚዳንቱም ኮሎኔል ጆንሰን ብራውን የቅርብ ወዳጅነት ያላቸው በመሆኑ በስጦታው መደሰታቸውን አምባሳደር ታዬ አስረድተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ቀናት በላይ ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን፤ በቆይታውም በተለያዩ ተቋማት በመገኘት በትምህርት ዙሪያ ገለጻ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የፓን አፍሪካ የቴክኒክ ማኅበር መሥራች ያው ኤፍ ኤል ዴቪስ በበኩላቸው፤ ማኅበሩ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዓመታት ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።