የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 22/ 2004/ ዋኢማ/ – የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዲሱ አዋጅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ አምባውና በሚኒስቴሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እስራኤል ተስፋዬ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አዲሱ አዋጁ የህዝብና የመንግስት ሀብት የሆነውን መሬት እኩል ተጠቃሚነት ከማረጋገጥና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

አዲሱ አዋጁ ሊወጣ የቻለው የህብረተሰቡን ፍላጎትና ጥቅም መሰረት በማድረግ መሆኑን ጠቁመው፤ አዋጁም የህብረተሰቡን ጥቆማ መሰረት በማድረግ መውጣቱን ገልፀዋል።

በህዝብ ሃብት እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ይህን ሃብት በመሸጥና በመለወጥ ያልተገባ ጥቅም የሚያጠራቅሙ ግለሰቦችን ለመከላከል እንደሚያስችልም ተገልጿል።

አዋጁ ለህብረተሰቡና ለአልሚዎች ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን አመልክተው፤ የማንኛውንም ህብረተሰብ መብት የሚጋፋ እንዳልሆነም በመግለጫው ተጠቁሟል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከዘጠኝ መቶ በላይ ከተሞች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፤ አንድ ከተማም ቢያንስ ከ2ሺ በላይ የሚሆን ነዋሪ በከፊል መተዳደሪያው ከግብርና የተለየ መሆን ተጠቁሟል።

አዲሱ አዋጅ ባለፈው መስከረም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀ ሲሆን፤ ነባር ባለይዞታዎችንና በውርስ የተላለፉ መሬቶችን የማይመለከት መሆኑን ገልፀው፤ ማንኛውም የከተማ ቦታ በሊዝ ብቻ የሚሸጥ መሆኑን ይደነግጋል ተብሏል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች መሬትን በመግዛትና አጥረው በመያዝ ከፍተኛ በሆነ ገንዘብ በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም ሲሰበስቡ የነበሩ ግለሰቦች ከአሁን በኋላ እንደማያዋጣቸውም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሸን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ደሳለኝ አምባው ተናግረዋል።

ይህ ሲባል ግን በህጋዊ መንገድ የተገኘ የይዞታ መብትና በነባር ይዞታ ላይ ያለ ንብረት ለ3ኛ ወገን አይተላለፍም ማለት እንዳልሆነ ገልፀው፤ የመብትና የንብረት ማስተላለፍ ጥቅሞች በአዲሱ አዋጅ የራሳቸው ስርዓት ተዘጋጅቶላቸዋል በማለት አስታውቀዋል።

አዲሱ አዋጅ ለተሳለጠ፣ ለውጤታማ፣ ለፍትሐዊና ለጤናማ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት ገበያ ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠቅም ሲሆን፤  ቀጣይነት ለተላበሰ የነፃ ገበያ ሥርዓት መስፋፋት፣ ግልጽና ተጠያቂነት ለሰፈነበትና የመሬት ባለቤቱንና የመሬት ተጠቃሚውን  መብቶችና ግዴታዎችን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት የመልካም አስተዳደር መኖር እጅግ መሠረታዊ ተቋማዊ ፍላጐት መሆኑንም በመግለጫው ወቅት መገለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።