የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንዲሳካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምቹ አካባቢያዊ እና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አባባ፣ ቅምት 29/2004 (ዋኢማ)– የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2004 በጀት አመት ውጤት ተኮር እቅድ ሶስት ቁልፍ መነሻዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገለጸ።ሀገራዊ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ የመስሪያ ቤቱ የ5 አመት ስትራቴጂካዊ እቅድ እና የመስሪያ ቤቱ የ2003 በጀት አመት አፈጻጸም፡፡

ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በማበርከት ተደማጭነትን ማጠናከር፣ የአደጋ ምንጮችን መቀነስ፣ አገራዊ ገጽታን መገንባት፣ የዲያስፖራውን የልማት ተሳትፎና ጥቅም ማሳደግ እና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎችን ደግሞ የበጀት አመቱ ስትራቴጂያዊ ግቦች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በማጠናከር ረገድ ሀገሪቱ በበጀት አመቱ ከ16 ሀገሮች ጋር ያለትን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማጠናከር፣ 6 አዳዲስ ስትራቴጂያዊ አጋሮችን ማፍራት፣ ከ36 አጋሮች ጋር ስምምነት መፈራረም ከስትራቴጂያዊ አላማዎች መካከል የተወሰኑት ናቸው፡፡

ሀገሪቱ በበጀት አመቱ ለአፍሪካ አህጉር ልማትና ዕድገት ተፅእኖ ባላቸው መድረኮች ተሳትፎዋን ታሳድጋለች፡፡ ለአረንጓዴው የሀይል ልማት አቅጣጫ የፋይናንስና የፖለቲካ ድጋፍ ለማስገኘት ትሰራለች ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ፡፡

የሀገሪቱ የልማት እቅድ እንዲሳካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመቻቸ አለምአቀፋዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታን ይፈጥራል ያሉት አቶ ሀይለማሪያም ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላም መስፈን የመሪነት ሚናውን ትወስዳለች ብለዋል፡፡

በተለይ የኤርትራን መንግስት አፍራሽ ተግባር ለማስቆም እና ለሱማሊያ፣ ለደቡብ ሱዳን እንዲሁም ለሌሎች ሀገራት መረጋጋት የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያሉት፡፡

በገፅታ ግንባታ ዙሪያም ከአለም አቀፍ እና አገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ብሎም በሴቶችና ህፃናት ዙርያ ከሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ የመስራትና መረጃን የመለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አላማ መንደፉንም ተናግረዋል፡፡

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂያዊ ግብም ትኩረቱ ሀገራዊ እቅዱን በማሳካት ላይ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ አስረድተዋል ፡፡