አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2004/ ዋኢማ/ – በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው 24 ግለሰቦች የተከላካይ ጠበቆቻቸውን አሟልተው ባለመቅረባቸው ለህዳር 13 ተቀጠረ።
አንደኛ ተከሳሽ አንዱአለም አራጌ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ናትናኤል መኮንንና ሰባተኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ የተከላካይ ጠበቃ በመያዝ በችሎቱ ሲገኙ፤ መንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ቀደም ባለው ችሎት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠላቸው አራት ተከሳሾች የተከላካይ ጠበቃ ባለመመደቡ ብቻቸውን ቀርበዋል።
አምስተኛ ተከሳሽ የሆነው ክንፈሚካኤል ደበበ በበኩሉ የተከላካይ ጠበቃ ለማቅረብ ተጨማሪ ቀጠሮ ጠይቋል።
በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው 16 ተከሳሾችም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በጋዜጣ ጥሪ መቅረቡን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
ክሱ ከተመሠረተባቸው 24 ግለሰቦች መካከል አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ እስክንድር ነጋና ሌሎች አምስት ተከሳሾች በህግ ጥላ ስር ሆነው የክስ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፤ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ መስፍን አማን፣ ኮሎኔል አለበል አማረ፣ መስፍን ነጋሽና አብይ ተክለ ማርያም በሌሉበት ከተከሰሱ 16 ተከሳሾች መካከል ይገኙበታል።
ተከሳሾቹ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪ ድርጅትነት ከተፈረጁት ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግና ከኤርትራ መንግስት ጋር በመሆን የሽብር ድርጊቶችን ለመፈፀም ተንቀሳቅሰዋል በሚል አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸው ሲሆን፤ ከተከሰሱባቸው ስድስት ክሶች መካከልም ከፍተኛ የሀገር ክህደትና ስለላ ይገኝበታል።
ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት የተከሳሾችን ክስ ለመስማት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም፤ የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ ተሟልተው እንዲቀርቡ ለህዳር 13 /2004 ዓ.ም ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ መጠናቀቁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።