በደቡብ ክልል ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የኦንኮሰርኪያስስ የዓይን ሕክምና ተሰጠ

ሀዋሳ ህዳር 8/2004/ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል ለ1 ሚሊዮን 470 ሺ ሰዎች የኦንኮሰርኪያስስ የዓይን ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ::

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው፤ ሕክምናው የተሰጠው ካለፈው የሐምሌ ወር ጀምሮ በክልሉ የኦንኮሰርኪያስስ የዓይን በሽታ ጎልቶ በሚታይባቸው በሸካ፣ በከፋና በቤንች ማጂ ዞኖች ነው::

በዞኖቹ በሚገኙ 25 ወረዳዎችና የገጠር አካባቢዎች የኦንኮሰርኪያስስ በሽታ ዋንኛ የጤና ችግር መሆኑን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ያለው አባተ ገልጸው፤ በሽታው ወደ ዓይነ-ሥውርነት ደረጃ ሳይሸጋገር ከወዲሁ ለመከላከል ሕብረተሰብ መራሽ የእንክብል መድሃኒቶች ዕደላ መከናወኑን ባለሙያው አስረድተዋል::

የሕክምና አገልግሎቱ በወረዳዎቹ በሚገኙ ክሊኒኮችና የጤና ጣቢያዎች ውስጥ የተሰጠው የክልሉ መንግሥት ጤና ቢሮ ከአጋር የጤና ድርጅቶች ባገኘው የገንዘብና የመድኃኒት ድጋፍ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል::

ቢሮው የኦንኮሰርኪያስስ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ ወረዳዎች እየተሰጠ የሚገኘውን የሕክምና አገልግሎት ለማስፋፋት በኦንኮሰርኪያስስ ሕክምና በመስጠት ላይ የሚሠሩ የጤና በጎ ፍቃደኛ አገልጋዮች መመልመልን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚኝ አመልክተዋል::

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኦንኮሰርኪያስስ በሽታ የሚከሰተው በወንዝ ዳርቻዎችና በረግረጋማ አካባቢ በሚገኙና ፍላሪያ በተባሉ ጥቁር ዝንቦች አማካኝነት ነው ::

ዓይንንና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን በማሳከክ የሚጀምረው ይኸው በሽታ በወቅቱ ሕክምና ካልተደረገለት ለዕድሜ ልክ ዓይነ-ሥውርነት ሊዳርግ እንደሚችል የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያውን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያመለክታል::