አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2004/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችላትን አዲስ ስትራቴጂ ይፋ አደረገች።
በሚቀጥሉት 20 አመታት በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ለመገንባት እስከ 150 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ያስፈልጋል።
የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ስትራቴጂው ትናንት በሂልተን ሆቴል ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ እንደማንኛውም አገር ሁሉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችላትን እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናት።
ስትራቴጂው የተበከለ የአየር ልቀትን በመቀነስና ተስማሚ የእድገት መንገድን በመከተል ኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት የሚረዳት መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ ስትራቴጂ እኤአ በ2025 ኢትዮጵያ መካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ ለመድረስ እና የኢኮኖሚ እድገቷ ከካርቦን ልቀት ነጻ ሆኖ አስተማማኝና ዘላቂ ሆኖ እንዲያድግ አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ይጠቅሳል።
ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል የሰብልና የቀንድ ከብት ምርትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና እና ገቢ በከፍተኛ ደረጃ በማረገጋጥ በአንጻሩ ደግሞ የበካይ ጭስ ልቀትን መቀነስ፣ የተቃጠለ አየርን ለመቋቋም እና ኢኮኖሚያዊና ስነ ምህዳራዊ ሚዛኑን ለመጠበቅ ውጤታማ የሆነ የደን መልሶ ማልማትና የደን ጥበቃ አስተዳዳርን ማጠናከር ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ኃይልን የማመንጨት አቅምን በማስፋፋት ለአገር ውስጥና ለጎረቤት አገራት ገበያ ማቅረብ፣ ዘመናዊና እና ብቃት ያለው የኤሌክትሪክ አጠቃቀምን ማሳደግ፣ በኢንዱስትሪ ተቋማት፣ በትራንስፖርትና በህንጻዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚሉት የስትራቴጂው ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው።
ዶክተር ተወልደብርሃን እንዳሉት ስትራቴጂው ኢትዮጵያ ከ15 አመታት በኋላ ወደ ከባቢ አየር የምትለቀው የበካይ ጭስ ልቀት ዜሮ ለማድረግ ያስቀመጠቸውን እቅድ ለማሳካት የማይተካ ሚና አለው፡፡
የተቃጠለ የካርቦን አየር ልቀትን ለመከላከል የሚወሰደው ኢኒሽዬቲቭ ጥራት ያለው ንጹህ ውሃና አየር እንዲኖር በማድረግ የህዝብ ጤና ማሻሻል፣ በገጠር ደግሞ የዳበረ አፈር ይዘትን በማሻሻልና የግብርና ምርቶችን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዝ ይሆናል።
በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 20 አመታት እነዚሀን ሁሉ ተግባራት በማከናወን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለመገንባት እስከ 150 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።
ገንዘቡ ለአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ከሚመደበው የበጀት ፕሮግራም፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኘው የአየር ንብረትን ፋይናንስ ይሸፈናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያም በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኘው የአየር ንብርት ፋይናንስ ድርሻዋን ለማግኘት ሁኔታዎችን የሚያስተባብር ብሔራዊ አመቻች ኮሚቴ አቋቁማለች።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪና የኢትዮጵያ ልማትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንዋይ ገብረአብ የአየር ንብረት ለውጥ ለኢትዮጵያ የወደፊት ችግር ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ያለ ተጨባጭ እውነታ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማትን መገንባት በእድገትና ትራስንፎርሜሽን እቅዱ ውስጥ ዋነኛ ግብ ሆኖ መካተቱን የገለጹት አቶ ንዋይ ስትራቴጂው የአየር ንብረትን በመቋቋም ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተጠጣጣመ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳካት የጋራ ግብና መሪ እቅድ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ከአረንጓዴ ልማት ጋር የተጣጣመ ኢኮኖሚን ለማሳካት፣ የመንግስት፣ የሲቪክ ማህብረሰብ፣ የምሁራን እና የመላው ህብረተሰብ የተቀናጀ ጥረትና እንቅስቃሴ አስፈላጊ መሆኑንም ኢዜአገ ልጿል።