ኢትዮ-ቴሌኮም የአገልግሎት አሰጣጥና አያያዝ ዘዴዎችን በመገምገም አገልግሎቱን እንደሚያሻሽል ገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 9/2004/ዋኢማ/– ኢትዮ-ቴሌኮም ኩባንያ የአገልግሎት አሰጣጡን ከደንበኞች ፍላጎት አንፃር በማጣጣም የአገልግሎት አሰጣጥና አያያዝ ዘዴዎችን በየጊዜው በመገምገም እንደሚያሻሽል አስታወቀ።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዦን ሚሸል ላቲዩት ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል ከኢትዮ- ቴሌኮም የኮርፖሬት ደንበኞች ጋር የተካሄደውን የውይይት መድረክ ሲከፍቱ እንደገለፁት፤  ኩባንያው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ሁሉም ህብረተሰብ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በየጊዜው የደንበኞች አያያዝ ዘዴዎችን መገምገም ይገባዋል።

በየጊዜው እያደገ የመጣውን የኮርፖሬት ደንበኞች ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ ለማርካት ኢትዮ-ቴሌኮም የተደራጀ ልዩ ድጋፍ ሰጪና ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲኖረው ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኩባንያው የደንበኞችን ፍላጎት ማዕከል ያደረገና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ጥራቱን ማሻሻልና በብቃት ማስተዳደር እንደሚገባው ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

ደንበኞች በአንድ ማዕከል ሁሉን አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማስቻል በቸርችር ጎዳና የቢዝነስ ማዕከል የከፈተ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋም ነክ ለሆኑ የኮርፖሬት ወይም ኢንተርፕራይዝ ደንበኞች ሁለገብ አገልግሎቶችን በጥራትና በቅልጥፍና ለመስጠት ኢትዮ-ቴሌኮም የኢንተርፕሬይዝ ዲቪዥንና የደንበኞች አገልግሎት ዲቪዥን መቋቋሙ አስታውሰዋል።

በመሆኑም የደንበኞችን ጥያቄ በማሰባሰብና በመገምገም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ ትኩረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውንና በተለያዩ አካባቢዎች  በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን የኦፕቲካል ፋይበር መስመር መቆረጥ አደጋ በማስቆም በኩል ደንበኞች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ስለኩባንያው የስራ አፈፃፀም፣ እቅድኘ አዳዲስ የአገልግሎት ማሻሻያዎች፣ በኔትዎርክ ማስፋፊያ ስራዎች፣ በአገልግሎት አስተማማኝነትና ጥራት፣ ከደንበኞች ጋር ስለሚደረግ የአገልግሎት አሰጣጥ ስምምነት፣ ስለ ደንበኞች አገልግሎትና የጥሪ መረጃ ማዕከል ገለፃ ተደርጓል።

በውይይቱ ላይም ከ350 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።