አክስዮን ማህበሩ የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎትን ለግሉ የንግድ ሕብረተሰብ መስጠት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2004/ዋኢማ/ – የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አክስዮን ማህበር ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ከጂቡቲ ወደብ እስከ አገር ውስጥ ባሉ ወደቦች የማድረስ /የመልቲሞዳል/ ትራንስፖርት አገልግሎት ለግሉ የንግድ ሕብረተሰብ መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

በአክስዮን ማህበሩ የማኔጂንግ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ያሬድ ሽፈራው፣ የሎጂስቲክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ዳኜ እና የሺፒንግ ሎጂስቲክስና ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ካልአዩ ተሰማ ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት አገልግሎቱ ከዩኒሞዳል አገልግሎት ጋር ሲነፃፀር የንግዱን ሕብረተሰብ ውጣ ውረድና ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ነው፡፡

አክስዮን ማህበሩ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የመንግሥት የልማት ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እቃዎችን ከተጫኑበት ወደብ እስከ ደረቅ ወደቦች ድረስ በመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም የተገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ በቅርቡ የግሉ ንግድ ሕብረተሰብም በመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ደንበኞች እቃቸውን ጂቡቲ ወደብ ለማንሳት ዋናውን የማስጫኛ ሠነድ ማቅረብ፣ የባሕር ትራንስፖርት ዋጋ መክፈልና በእቃው ላይ ተጣለውን ታክስ እና የየብስ ትራንስፖርት ዋጋ መክፈል ሳይጠበቅባቸው እቃቸውን በአጓጓዡ ሙሉ ኃላፊነት ወደ አገር ውስጥ ደረቅ ወደቦች ለማምጣት ይረዳል ብለዋል፡፡

የንግዱ ሕብረተሰብ ቀደም ሲል ይቀጠምበት የነበረው የዩኒሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ውሎችን ለማስፈፀም በርካታ ቢሮዎች መሄድን ጨምሮ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠበቅበት ነበር ብለዋል፡፡

የአገልግሎቱ መጀመር በደንበኞች ላይ ይደርስ የነበረውን ውጣ ውረድና የገንዘብ ጫና እፎይታ ከመስጠቱም ባሻገር በጂቡቲ ወደብ የሚጠየቁትን ከፍተኛ የመጋዘን ኪራይ በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የመልቲሞዳል አገልግሎቱ ይህን ውጣ ውረድ በማስቀረት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ እቃቸውን ካስመጡበት ወደብ ጀምሮ በአገሪቱ በሚገኙ ደረቅ ወደብ እስኪደርስ ድረስ ያሉትን ተግባራት አክስዮን ማህበሩ በአንድ ውል ብቻ ያከናውናል፡፡

አገልግሎቱም ቀደም ሲል ለዩኒሞዳል ከሚከፍሉት ክፍያ የማይበልጥ መሆኑን ኃላፊዎቹ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡