የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 31ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11 / 2004/ዋኢማ/ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 31ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው።

በዓሉ እየተከበረ ያለው የንቅናቄው አባላትና ደጋፊዎች፣ አጋር ድርጅቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሥልጣናትና የከተማ  ነዋሪዎች በተገኙበት ነው።

በተለይም በአዳማ  ከተማና አካባቢዋ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በዓሉ ሲከበር የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ባደረጉት ንግግር ታጋዮች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት ለመጣል ያሳዩትን ጽናትና ቁርጠኝነት አዲሱ ትውልድም በልማቱ  መስክ  ሊደግመው ይገባል ብለዋል።

የብአዴን 31ኛው ዓመት የምስረታ በዓል የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ውጤት ማሳየት በጀመረበትና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተፋጠነ ባለበት ወቅት  መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 31ኛ ዓመት በዓል በአምቦ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

ታጋዮች በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማስቀጠል አባላትና ደጋፊዎች ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የንቅናቄው አስተባባሪ አሳስበዋል።

አስተባባሪው አቶ መልካሙ  መንበር በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀ የፓናል ዉይይት ላይ እንዳሉት ታጋዮች በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን  ሰላምና ልማት ለማስቀጠል  አባላትና ደጋፊዎች  ጥረታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

በበዓሉ ላይ ለትግሉ ሰማዕታት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት መካሄዱንም የኢዜአ ዘገባን ጠቅሶ ኤፍቢሲ ዘገባ ያስረዳል።