አዲስ አበባ ህዳር 13/2004/ዋኢማ/– በሶማሊያ የሽግግር ምክር ቤት ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ሃሰን ሼክ አደን የተመራው የልዑካን ቡድን ከኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ጋር በሁለት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡
በኬንያና በተቀረው አለም አቀፍ ማህበረሰብ እርምጃ የአልሸባብ በደቡብ ሱማሊያ መዳከምና የሱማሊያ የሽግግር ምክር ቤት ፓርላማን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ መሪ ሃሰን ሼክ አደን በሀገሪቱ የተረጋጋ መንግስት ለመመስረት በሚደረገው ጥረት ሁሉንም ህብረተሰብ ያማከለና አቅሙ የጎለበተ ፓርላማ እንደሚያስፈልገን እምነት አለን ብለዋል፡፡
ይህ እንዲሆንም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁት አፈ-ጉባዔው፤ «በኢትዮጵያና በሱማሊያ ፓርላማ መካከል ትብብር በመፍጠር የኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲረዳን እንፈልጋለን፡፡ እሱም አቅማችንን ይበልጥ ይገነባዋል፡፡» በማለት አፈ-ጉባዔው ተናግረዋል።
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በተናጠልም ይሁን በኢጋድ በኩል ባለው የፓርላማዎች ህብረት የሽግግር መንግስቱን ፓርላማ አቅም ለመገንባት ድጋፏን እንደምታደርግ የገለፁ ሲሆን፤ የተቋሙ መጠናከር ለወደፊቷ ሱማሊያም ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን የፀጥታ ጉዳይ አንስተው የተናገሩት ሃሰን ሼክ አደን ሞቃዲሾ ሙሉ ለሙሉ በሽግግር መንግስቱ ቁጥጥር ስር እየዋለች መሆኑን ተናግረው፤ በደቡብ ሱማሊያ ጁባ የዘመቱት የኬንያ ኃይሎችም አበረታች ውጤት አስመዘግበዋል ብለዋል።
አልሸባብ የተረጋጋችና መንግስት ያላትን ሱማሊያ እንደማይፈልግ ህዝባዊ መሰረት የሌለው መሆኑንም አለም አቀፍ ማህበረሰብ ተገንዝቧል በማለት ሃሰን ሼክ አደን ገልፀዋል።
አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በአሁኑ ሰዓት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሽግግር መንግስቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍና ደቡብ ሱማሊያ እየተገኘ ያለውን ውጤት ወደ መልካም አጋጣሚ ልትቀይሩት ይገባል ብለዋቸዋል፡፡
ህዝባዊ መሰረት የሌለውን አልሸባብ ለማስወገድና በሱማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሳኙ መፍትሔ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደጋጋሚ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የሽግግር መንግስቱ መጠናከር ነው ሲሉ አፈ-ጉባኤ አባዱላ መግለፃቸውን ኢሬቴድ ዘግቧል።