የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነታቸውን አጥብበው የሀገሪቱን አምባገነን ስርዓት እንዲያስወግዱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ህዳር 13/2004/ዋኢማ/– የኤርትራ ኮሚሽን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነታቸውን አጥብበው የሀገሪቱን አምባገነን ስርዓት እንዲያስወግዱ ጥሪ አቀረበ።

የኤርትራ ኮሚሽን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሊቀመንበር አምሃ ዶሞኒካ ፍትህና ዴሞክራሲ የናፈቀውን የኤርትራን ህዝብ ከአምባገነን ስርዓት የማላቀቂያው ጊዜ አሁን በመሆኑ የስርዓቱ ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን በማጥበብ የኤርትራን ህዝብ እንዲታደጉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኤርትራን መንግስት አስከፊ ስርዓት ለማስወገድ የሚያስችል አዲስ የስትራቴጂ ትግል የሚቀይስ “የኤርትራ ብሔራዊ ጉባዔ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ” ውይይት በሐዋሳ ከተማ ሲጀመር፤ የኤርትራ ህዝብ የጭቆና አገዛዝን በመቃወም ለበርካታ ዓመታት የታገለ ቢሆንም ከነጻነትም በኋላ በአምባገነን ስርዓት ለመገዛት ተገዷል፡፡

የኤርትራ መንግስት በሚከተለው የአፈና አገዛዝ ሀገሪቱ የሰብአዊ መብት የሚረገጥባትና ዜጎች በአፈና እና በፍርሃት የሚኖሩባት ሀገር ለመሆን መብቃቷን ገልፀው፤ የስርዓቱ ተቃዋሚዎች ልዩነታቸውን በማጥበብ አንድ መሆን እንደሚገባቸው ተገልጿል።

በጉባዔው የኤርትራ ኮሚሽን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ባለፉት 16 ወራት የደረሰበትን አፈጻፀም ይገመግማል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትን አቋም ያቀረቡት የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በኤርትራ ህዝብ ጫንቃ ላይ የተጫነውን አምባገነን አገዛዝ ለማስወገድ የተለያዩ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች አመርቂ ውጤት ማግኘት አልቻሉም፡፡

በመሆኑም የተጀመረው ጉባዔ የነበሩትን ችግሮች በማስወገድ የጋራ ግንዛቤና መግባባት ላይ እንደሚደርስ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በኤርትራ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማስፈን ለሚደረገው ትግልም ወንድም የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደማይለየውም ተገልጿል።

በጉባዔው የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች መልእክት ሲያስተላልፉ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ ኤርትራውያን ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ጉባዔው ለሰባት ቀናት እንደሚቆይም የኤሬቴድ ዘገባ ያስረዳል።