አዲስ አበባ ህዳር 13/2004/ዋኢማ/ – የአፍሪካ ሀገራት በአለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን ያለቀላቸውን ምርቶች ወደ ውጪ መላክ እንደሚገባቸው ተገለፀ፡፡
ይህ የተገለፀው የአፍሪካ ገበያ ፎረም አዲስ አበባ ላይ በተካሄደበት ወቅት ሲሆን፤ በፎረሙ ላይ ሁለት አከራካሪ ሃሳቦች ጎልተው ወጥተዋል፡፡
አህጉሪቱ አሁን ያላትን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ አራት መሰረታዊ የቤት ስራዎች በሀገራት ሲከናወኑ ብቻ ነው የተፈለገው ለውጥ የሚመጣው የሚለውን ሃሳብ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ማንያዘዋል አስረድተዋል፡፡
“በመጀመሪያ ደረጃ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ወደ ውጪ የምንልከው ጥሬ ዕቃ ነው፡፡ የሀገር ውስጥና የውስጥ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ጥሬ ዕቃዎቹን እዚሁ ወደ አለቀለት ምርት መቀየር አለብን፡፡” ያሉት ሚኒስትሩ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሸጋገር የተለያዩ እስትራቴጂዎችን ነድፈን መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል፡፡
እነዚህ የቤት ስራዎች ሳይከናወኑ እንዴት የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚቻልም ጥያቄ አቅርበዋል።
በፎረሙ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ኦኪሺ አድባጎ በበኩላቸው፤ ዋናው አስፈላጊው ነገር የገበያ ፖሊሲ ለውጥና ነጻ ገበያ በአህጉሪቱ ሲዘረጋ ነው ብለዋል፡፡ “አፍሪካ ሃብታም አህጉር ነች፡፡ ያልተነካ ማዕድንም ባለቤት ነች፡፡ እነዚህን የሰውና የተፈጥሮ ሀብት በማቀናጀት ሀብት መፍጠር ይቻላል፡፡ የገበያ ትስስርም እንዲሁ፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገው ወጥ የሆነ የገበያ ፖሊሲና የነጻ ገበያ ስርዓትን በአህጉር ደረጃ ማስፈን ነው፡፡” በማለት ዶክተሩ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ አብዱላሂ ጃኔ ደግሞ ክፍለ አህጉራዊ የገበያ ትስስርን በማጠናከር ወደ አህጉራዊ የገበያ ጥምረት ማቅናት እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
የኢኮኖሚ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ማህበር ያለው የገበያ ትስስር እድገቱ ይቀጥላል፡፡ ለአብነት ያህል የምስራቅና የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ /ኮሜሳ/ን ያነሱት ዋና ፀሃፊው የገበያ ትስስሩ በ35.4 በመቶ ማደጉን ገልፀዋል፡፡ “በአንድ አመት ውስጥ አባል ሀገራቱ የ5 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ የንግድ ልውውጥ አከናውነዋል፡፡
በአስራ ዘጠኝ አገራት ደግሞ የወጭ ንግድ ከ20 እስከ 70 በመቶ አድጓል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ምክንያቱ የአካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማህበር በማጠናከር ወደ አህጉራዊ ጥምረት በሂደት መሸጋገር ወሳኝ አቅጣጫ ነው፡፡” ሲሉ ዋና ፀሃፊው አብዱላሂ ጃኔ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ወደ ውጪ የምትልካቸው ምርቶች በግብርናው ዘርፍ ላይ መንጠላጠላቸው፤ አይነታቸውም ውስን መሆኑ፤ በግብይት ሂደቱ ላይ ያለው ረጅም ሰንሰለትና የክፍያ ኋላቀርነት፣ የተሟላ የመሰረተ ልማት በአህጉሪቱ አለመኖሩ ገበያውን ከሚፈታተኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ ተጠቁሟል በፎረሙ ላይ፡፡ አፍሪካ ከአለም አቀፉ ገበያ የሚያጋጥማት ችግር ደግሞ እየተፈታተናት እንደሚገኝ ተወስቷል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በዋነኝነት ሀገራት ለሀገራት የሚያደርጉትን የንግድ ልውውጥ ማጠናከር ይገባል ማለታቸውን የኢሬቴድ ዘገባ ያስረዳል።