አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2004/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህዳር 18 እስከ 22 ቀን 2004 ዓ.ም የሚቆይ የአፍሪካ ኮሚሽን የግብርና ስታቲስቲክስ ጉባኤ እንደምታስተናግድ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄደውን ጉባኤ የሚያዘጋጁት የማዕከላዊ ስታቲስቲከስ ኤጀንሲ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የዓለም ምግብ ድርጅትና የአፍሪካ ኢኮኖሚከ ኮሚሽን የስታቲስቲክስ ማዕከል በጋራ በመሆን ነው፡፡
በስብሰባው ላይ ሰለ ተሻለች አፍሪካ የወደፊት ዕድገት ዕውን ለማድረግ በሚያስችሉ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በሚመለከተቸው ባለሙያዎች የተለያዩ ጥናታዊ ወረቀቶች እንደሚያቀርቡም ኤጀንሲው አመልክቷል።
በአየር ንብረት አጠባበቅ ላይም ሰፊ ውይይት እንደሚደረግና በዚሁ ጉባኤ መክፈቻ ቀንም በየዓመቱ ህዳር ወር ላይ ሰለሚከበረው የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ቀን፣ የአገራዊው የግብርና ስታቲስቲክ የሰብል ምርቶችንና በሌሎች ተዛማጅ ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ ከሁሉም የዓለም አገሮች በሚመጡ ተሳተፊዎች ውይይት እንደሚደረግም ይጠበቃል ሲል የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።