ህገ-መንግስቱ የሁሉንም ክልሎች እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጡ ተገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 14/2004/ዋኢማ/ – ዜጎች መክረውና ተወያይተው ያፀደቁት ህገ-መንግስት የሁሉንም ክልሎች የእኩል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መምጣቱን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ገለፁ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በቅርቡ ህዳር 29 የሚከበረው ህገ-መንግስቱ የፀደቀበትና የብሔር ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሁሉንም ክልሎች በልማቱ እኩል ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ነው።

ሰፊና መሰረት ያለው ለውጥ ለማምጣት የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የገለፁት ዶክተር ሽፈራው፤ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ህገ-መንግስቱም ይህንን እንደሚደነግግ ገልፀው፤ ዜጎችም በያሉበት አካባቢ የልማት አፍላቂ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ቀደም ባሉት ስርዓት ዜጎች በሀገሪቱ የእኩል ተጠቃሚነት እንዳልነበረ የስታወሱት ዶክተር ሽፈራው፤ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ግን የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መምጣቱን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው የ11 በመቶ እድገት የህገ-መንግስቱ የእኩል ተጠቃሚነት ውጤት ማሳያ ነው በማለት ገልፀዋል።

በሚቀጥሉት ዓመታትም ድህነትን ታሪክ ለማድረግ መላው ህብረተሰብ የራሱን አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዜጎች ቀደም ባሉት አመታት ያስጨንቃቸው የነበረውን የማንነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄም ህገ-መንግስቱ ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል።

ህገ-መንግስቱ በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔር ብሔሮችና ብሔረሰቦች ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ባስቀመጠው መሰረት ክልሎቹን ለማገዝ የሚያስችሉ በፌዴራል መንግስት ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ገልፀዋል።

በፌዴራል ደረጃ ልዩ የእገዛ ቦርድ በማዋቀር ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ዋና ዋና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ በማነጣጠር የማስፈፀም አቅማቸውን የማሳደግ ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም የልማት ስራውን ሊያሳካ የሚያስችል አደረጃጀት በመፍጠር በእቅድ እንዲመሩ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራበት መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህም የህዝቡን በልማት ላይ ያለው ተሳትፎ እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል ያሉት ዶክተር ሽፈራው፤ በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን በመያዝ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።