አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2004/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የምታደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አረጋገጡ።
ሚኒስትሩ አቶ ሃይለማሪም ደሰላኝ ከሶማሊያ ፌዴራል የሽግግር መንግስት አፈ-ጉባኤ ሸሪፍ ሐሰን ሼክ ኤደን ጋር ባደረጉት ውይይት እንዳሉት በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ከዚህ ቀደም የምታደርገውን ድጋፍ ይበልጥ ታጠናክራለች።
በአልሻባብ ላይ የሚወሰደው እርምጃ የተናጠል ሳይሆን የኢጋድ አባል አገራት፣ በአፍሪካ ህብረት በአለም አቀፉን ማህበረሰብ የጋራ ተሳትፎ መሆን እንዳለበትም መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳዳር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የሶማሊያ ፌዴራል የሽግግር መንግስት አፈ-ጉባኤ ሼክ ሸሪፍ ሐሰን ሼክ ኤደን ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ውይይቱ በሶማሊያ ስላለው ረሀብ፣ ድርቅና የጸጥታ ሁኔታ ይበልጥ ትኩረት ያደረገ ነበር።
በሶማሊያ ያለውን ቀውስ ዘላቂ እልባት ለመስጠት በዩጋንዳ ርእሰ መዲና ካምፓላ የተደረሰውን የካምፓላ ስምምነት ገቢራዊነት በሚመለከትም ውይይት ተካሂዷል።
በዩጋንዳ ካምፓላ የተደረሰው ስምምነት በሶስት ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ አልሻባብን በጋራ መታገል፣ የሶማሊያ ሽግግር መንግስቱን ጊዜ በማፋጠን የካምፓላን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ፣ አልሻባብ በሂደት በሚለቃቸው ቦታዎች ላይ የሲቪል አስተዳደር መመስረት የሚሉት ይጠቀሳሉ።
የሽግግር መንግስቱና የአካባቢው አገራት አልሻባብንና ለሌሎች የታጠቁ ሃይሎችን ለማዳከምና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በጋራ መስራት በሚቻልበት ጉዳይ ላይም ውይይት ተካሂዷል።
አፈ-ጉባኤው በቀጣዩ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በሶማሊያ በሚካሄደው ምርጫ ላይ የኢትዮጵያንና የኢጋድ አባል አገራትን ድጋፍንም ጠይቀዋል።
በሶማሊያ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የፓርላማ አባላት ቁጥር አቅጣጫ ማስያዝ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሂዳል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።