የህዳሴ ጉዞ የሚሰምረው ህብረተሰቡ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት ሲከላከል ነው-ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2004/ ዋኢማ/–  የህዳሴ ጉዞ የሚሰምረው ህብረተሰቡ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት በመከላከልና በማስቆም ልማታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው መሆኑን ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ የነጭ ሪቫን ቀንን ምክንያት በማድረግ ትናንት ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የነጭ ሪቫን ቀን ዘንድሮ በሃገራችን ለ6ኛ ጊዜ “ፆታዊ ጥቃትን በማስቆም የህዳሴውን የልማት ጉዞ እናፋጥን” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት ይህን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የበዓሉ ዋና ዓላማም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወንዶች የድርሻቸውን እንዲወጡ መነሳሳትን ለመፍጠር ነው፡፡

ወንዶች በግላቸው ጥቃትን ያለመፈፀም ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወንዶች የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቀረትም ጭምር ቃል የሚገቡበት ዕለት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የህብረተሰቡ ግማሽ አካል በሆኑት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ችላ በማለት እድገትን መጠበቅ የማይታሰብ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ቀጣይነት ያለው ልማት ማምጣት የሚቻለው ሴቶች በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ በእኩልነት ሲሳተፉ ብቻ በመሆኑ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ የሚገድበውን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል የህብረተሰቡ በተለይም የወንዶች አጋርነት ከምንግዜውም በበለጠ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የፆታዊ ጥቃት ግንባር ቀደም ተጎጂዎች እናቶች፣ እህቶች፣ ሚስቶችና ልጆቻችን ስለሆኑ ጥቃቱ የሚያስከትለው ጉዳት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ ነው ብለዋል ፡፡

በመሆኑም ጥቃቱን በመከላከሉ ተግባር ወንዶች በግንባር ቀደምትነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

የሴቶች ፆታዊ ጥቃት መንስኤዎች ኋላ ቀር የሆኑ ባህላዊ አስተሳሰቦችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመሆናቸው በሴቶች ላይ ሲፈፀሙ የሚያስከትሉት ጉዳት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሴቶች ፆታዊ ጥቃት ሲደርሰባቸው ኤች አይ ቪ/ኤድስን ጨምሮ ለአባለዘር በሽታዎች መጋለጥ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ውርጃና ከውርጃ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች፣ የሥነ ልቦና አለመረጋጋት፣ በወሊድ ወቅት ለአደጋ መጋለጥና የመሳሰሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡

የሴቶችን ጥቃት ማስቆም ለሴቶች ወይም ለሴቶች ማህበራት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊሳተፍበት የሚገባ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአካባቢ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና በፆታ ላይ የተመሰረቱ የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም ጉልህ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

ሴቶችም ችግሮቻቸውን በጋራ ለማስወገድና የሚደርስባቸውንም የኃይል ጥቃት በጋራ ለመከላከል ህገ መንግሥቱ ባጎናፀፋቸው የመደራጀት መብት በመጠቀም ጥቅማቸውን ለማስከበር ተፅዕኖ ማሳደር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡