የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉም ሃላፊቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2004/ዋኢማ/–  የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉም ሃላፊቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጅማ ፋናኤፍ ኤም 98 ነጥብ 1 በቡና ጥራትና የቁጠባ ባህል ዙሪያ ያተኮረ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደበት ወቅት ነው ጥሪው የቀረበው።

የኤፍቢሲ ፕሮግራም ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል እንዳለ ውይይቱን በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት የመድረኩ መካሄድ ኤፍቢሲ የተመሰረተበትን 17ኛ ዓመት ባከበረበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

ፋና በህብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሆነና ስለቡና ጥራትና ቁጠባ እንዲህ ዓይነቱ የውይይት ምክክር መደረጉ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ገቢ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

የጅማ ዞን ምክትል አስተደደሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስዩም ኢታና የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ኤፍቢሲ ዘገባ ያስረዳል።